የሥራ ዕድሎች ክህሎት መር እንዲኾኑ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

41

አዲስ አበባ: መጋቢት 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢንተርፕራይዞች የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ክህሎት መር እንዲኾኑ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ አስታውቋል። ቢሮው ወደ መካከለኛ ደረጃ የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞችን የምረቃ መርሐ ግብር አካሂዷል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ጥራቱ በየነ ባለፉት ዓመታት ኢንተርፕራይዞችን ማዕከል አድርጎ በመሥራት የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ክህሎት መር እንዲኾኑ እየተሠራ ነው ብለዋል። ኢንተርፕራይዞቹ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በገበያ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ እንዲኾኑ በማድረግ እና ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን በማስቀረት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ የኢንተርፕራይዝ እና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኀላፊ መሐመድ ልጋኒ ከአንደኛ እስከ 12ኛ ዙር ድረስ በነበረው የሽግግር ሂደት 2 ሺህ 241 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ደረጃ መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሸጋገሩት 13ኛ ዙር 281 ኢንተርፕራይዞች ናቸው። ኢንተርፕራይዞቹ ለሽግግር የተቀመጠውን መስፈርት ያሟሉ ናቸው ተብሏል። ተጨማሪ 156 ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም ወደ አምራች ዘርፍ ሽግግር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በሥራ እና ክህሎት ቢሮው ዛሬ ወደ መከካለኛ ደረጃ ሽግግር ያደረጉት ኢንተርፕራይዞቹ ወደ ኢንዱስትሪ ቢሮ ተላልፈው በዛም አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው የተሻለ አቅም እና ሃብት የሚያፈሩበት ዕድል ይመቻቻልም ተብሏል።

ዘጋቢ: ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኀይል ስርቆት በሕዝብ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እና የሕግ ተጠያቂነቱ?
Next articleሴቶች በሀገር ልማት እና በዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ቁልፍ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል።