የኀይል ስርቆት በሕዝብ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እና የሕግ ተጠያቂነቱ?

42

ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራት ያላቸውን መዋዕለ ንዋይ አፍስሰው ለዜጎቻቸው የሚበጁ መሠረተ ልማቶችን ያቀርባሉ። መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የሚውለው ገንዘብ ከዜጎች ላይ ከሚሠበሠብ የገቢ ግብር፣ አለያም ደግሞ ነገ በሀገር የእዳ መዝገብ ላይ ከሚሰፍር ብድር የሚገኝ ነው። በየትኛውም መንገድ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ሕዝቡን በአግባቡ እንዲያገለግሉ እና ለግንባታ የፈሰሰውን ወጭም ዞረው ይተኩ ዘንድ ማንኛውም አካል ጤነኛ የኾነ የአጠቃቀም ዘዴን ይከተል ዘንድ ግድ ይላል።

ኢትዮጵያ ለሕዝብ አገልግሎት ሰጭ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የምትታትር ሀገር ናት። ወዲህ ደግሞ የተገነቡ እና በመገንባት ላይ ባሉ ልማቶች ላይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችም ይስተዋላሉ። በኤሌክትሪክ፣ በውኃ፣ በቴሌኮም እና በሌሎችም አገልግሎቶች ላይ የተለያየ ሥርቆት ይፈጸማል።

በዛሬው የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ የሕግ ጉዳይ ዝግጅታችን በተለይም የኤሌክትሪክ ኀይል ስርቆት ምንነትን እና የሕግ ተጠያቂነቱን እንዳስሳለን። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕግ ዳይሬክተር እሸቱ በልሁ ማንኛውም ደንበኛ ቆጣሪ የሚገጠምለት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ውል ሲገባ ብቻ ነው። ቆጣሪው የቆጠረውን የኤሌክትሪክ ኀይል በመከታተል እና በማስላት መክፈል ግዴታ ነው ይላሉ።

የኤሌክትሪክ ኀይል የቀን ከቀን እንቅስቃሴዎቻችን ምን ያህል ወሳኝ ሚና እንደሚጫዎቱ ተገንዝቦ ይህንን ሀብት መንከባከብ እና በውሉ መሠረት በአግባቡ መጠቀም ከሁሉም ዜጎች የሚጠበቅ ኀላፊነት ነው። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የኀይል ሥርቆት እንደሚፈጸምም ተናግረዋል።

ማንኛውንም አይነት የኀይል ስርቆት የሚፈጽሙ ሕገ ወጥ አካላት በሕግ እንደሚጠየቁ በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዓዋጅ ቁጥር 810/2006 ከአንቀጽ 28 እስከ 30 ድረስ መቀመጡን ገልጸዋል። በዚሁ አዋጅ በተለይም በአንቀጽ 28 ስር እንደሰፈረው አንድ ሰው የኤሌክትሪክ ኀይል ሰረቀ የሚባለው:-

👉 በሕገ ወጥ መንገድ ከሌላ ጋር ካገናኘ
👉መስመር ካሰናከለ
👉 የኤሌክትሪክ ኀይል ኢንዲሰረቅ ከሌላ መስመር ጋር እንዲገናኝ ወይም መስመሩ እንዲሰናከል ካደረገ፣
👉 መስመሩ የተሰረቀ ከኾነ
👉 በሕገ ወጥ መንገድ ከሌላ መስመር ጋር ከተገናኘ
👉 የተሰናከለ መኾኑን እያወቀ ከዚሁ መስመር ማናቸውም የኤሌክትሪክ ኀይል ለፍጆታ ካዋለ ነው።

በእንዲህ አይነት የኀይል ስርቆት ወንጀል የተከሰሰ ሰው እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል ገልጸዋል። ወንጀሉ 20 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣም አብራርተዋል። ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ውል ገብቶ ቆጣሪ የወሰደ ወይም ደግሞ ሌላ ሰው በስሙ ካወጣው ቆጣሪ ኀይል የሰረቀ ሰው በሕግ ይጠየቃል።

ግለሰቦች ቆጣሪ የገባለትን ቤት ግዥ በሚፈጽሙ ጊዜ በቅድሚያ ወደአካባቢው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በማምራት ቆጣሪው ከወንጀል ድርጊት የጸዳ መኾኑን በማረጋገጥ ከወንጀል ተጠያቂነት መዳን እንዳለባቸውም አሳስበዋል። “ኀይል መስረቅ ማለት ሀገርን ወይም ደግሞ የራስን ኪስ እንደመስረቅ ነው፤ ሁሉም ሰው የኀይል ስርቆትን መከላከል አለበት” ነው የሚሉት። በተጠቀምነው የኤሌክትሪክ ፍጆታ ልክ አስበን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማንከፍል ከኾነ ተቋሙ ሊጠነክር፣ ተጨማሪ መሠረተ ልማቶችንም ሊገነባ አይችልም ነው ያሉት።

የኤሌክትሪክ ሥርቆት በሚፈጸም ጊዜ የኀይል መቆራረጥ ያጋጥማል፣ መሥመሮች ላይም ቃጠሎ ይደርሳል ብለዋል። ድርጊቱ የተቋሙን መልሶ የመገንባት አቅም እንደሚያዳክም እና ድምር ውጤቱም ሕዝብን ኀይል እንደሚያሳጣ አብራርተዋል።

“ለሰው ልጆች ሕይወት የኾነውን የኤሌክትሪክ ኀይል በአግባቡ ለመጠቀም ሕግን ማክበር እና ማስከበር ያስፈልጋል” ነው ያሉት። መሠረተ ልማትን መጠበቅ በሕዝብ ላይ የወደቀ ኀላፊነት ነውና የኀይል ስርቆት ሲፈጽም የተገኘን ግለሰብ መጠቆም እና ማረም እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኀይሌ (ዶ.ር) በአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ኮሚሽን የንቅናቄ መድረክ ላይ ለመሳተፍ ባሕርዳር ገቡ።
Next articleየሥራ ዕድሎች ክህሎት መር እንዲኾኑ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።