
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የትምህርት ንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በንቅናቄ መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች መማር ማስተማሩ ላይ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን የችግሩ ስፋት ጥልቅ ነው ብለዋል። ከክልሉ ሕዝብ እሴት ባፈነገጠ መልኩ መምህራን ይገደላሉ፣ ይታገታሉ፣ ይንገላታሉ ነው ያሉት። ከትምህርት የሚቀድም ተግባር የለም ብሎ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ልጆቻችን ይማሩ ብሎ ከመሪዎች ጋር መታገል እንደሚገባውም ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማስከፈት እና ሙሉ ለሙሉ ወደ መደበኛ ትምህርት ለማምጣት ብዙ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ባለመምጣታቸው ምክንያት ያለ ዕድሜያቸው እንዲያገቡ፣ ተስፋቸው እንዲጨናገፍ እየኾኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አንድ ኾነን በትምህርት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር መፍታት አለብን ነው ያሉት። ትልቁ አጀንዳችን ትምህርት ነው፣ አሁንም ተማሪዎች መመዝገብ እና መማር አለባቸው ብለዋል።
ለራሳችን ችግር ራሳችን መፍትሔ ፈልገን ተግባራዊ ሥራ መሥራት አለብን ነው ያሉት። የጥንት ታሪክ እና ዕውቀት ያለን ኾነን ሳለ በዚህ ዘመን በዚህ ልክ መውረድ ያሳፍራል ብለዋል። ልጆቻችን በነጻነት መማር መቻል አለባቸው ያሉት ተሳታፊዎቹ ትምህርት ከሁሉም ወገንተኝነት የሌለበት ገለልተኛ መኾኑንም ተናግረዋል።
ቀደምት የኾነው ሕዝብ አሁን ላይ በከፋ ችግር ውስጥ ነው ብለዋል። ትውልድ እንዳይማር ማድረግ በሀገር እና በሕዝብ ላይ መፍረድ መኾኑንም ገልጸዋል። ልጆቻችን በነጻነት እንዲማሩ የማድረግ ኀላፊነት እና ታሪካዊ አደራ አለብን ነው ያሉት።
መምህራን በነጻነት ማስተማር አለባቸው ብለዋል። የክልሉ ችግር የጋራችን ነው፣ መፍትሔውንም በጋራ ማመንጨት አለብን ነው ያሉት። ክልሉ ለተፈጠረበት የትምህርት ችግር ልዩ ድጋፍ እና ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።
ጥፋቱን በተገቢው መንገድ በመረዳት እና ከእኛ ውጭ ችግሩን የሚያስተካክለው የለም በሚል ቁርጠኝነት መሥራት ይገባናል ነው ያሉት። በቁርጠኝነት ከሠራን ከችግሮች መውጣት እችላለን ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት መጀመሪያ ችግሩን በግልጽ መረዳት ይገባል ብለዋል። ይህ ትውልድ እንዲህ አይነት አደጋ ሲገጥመው ዝም ብሎ አይቶ ማለፍ የለብትም፣ አደጋውን መፍታት ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል ነው ያሉት።
“የመጨረሻው ያለ መማር መገለጫው ትምህርት ላይ እንቅፋት መኾን ነው” ብለዋል። ትምህርት ቤቶችን መንካት ማለት ለአንድ አካል የመጨረሻው ከሕዝብ የሚጣላበት መንገድ መኾኑንም ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቶችን ኾን ብሎ ማጥቃት አጸያፊ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል። ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ የሚያደርግ ኀይል ሕዝብን ወደ ኋላ ይመልሳል እንጂ ወደፊት ማሻገር አይቻለውም” ብለዋል።
ትምህርት ቤቶች በምንም አይነት መልኩ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ መኾን የለባቸውም ነው ያሉት። አሁን ባለው ችግር ከቀጠልን በአማራ ሕዝብ የትውልድ ክፍተት መፍጠር ነው፣ የአማራ ሕዝብ እንዲህ አይነት ነገር ይፈቅዳል ብዬ አላምንም፣ መፍቀድም የለብትም፣ ፖለቲከኞች ፖለቲካቸውን በሜዳቸው ይጫወቱ ትምህርት ቤቶችን ግን መልቀቅ አለባቸው ብለዋል።
ለትምህርት ትልቅ ግንዛቤ እና ቦታ ያለው የአማራ ሕዝብ ይሄን አይነት አካሄድ መታገል ይገባዋል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!