
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የትምህርት ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው። በንቅናቄ መድረኩ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሰተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ትምህርት ሰብዓዊ ሃብትን ለማልማት ወደር የሌለው ዘርፍ መኾኑን ገልጸዋል። ዛሬ በሳይንስ እና ቴክኖሎጅ የበለጸጉ ሀገራት የዕድገት ሚስጥራቸው የሰው ሃብታቸውን በአግባቡ በማልማታቸው እና ለትምህርት ሥራቸው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው መሥራታቸው ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም ለትምህርት ልማት ዘርፍ በሰጠችው ትኩረት ባለፉት ዓመታት በትምህርት ተሳትፎ እና ተደራሽነት ትልቅ ለወጥ መመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በገጠመን ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች በኢትዮጵያም ኾነ በክልሉ የትምህርት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሟል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል በኮሮና ቫይረስ፣ በሰሜኑ ጦርነት እና ባለው የክልሉ የጸጥታ ችግር በትምህርት ተሳትፎ፣ ጥራት እና ፍትሐዊነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች እና የውስጥ ባንዳዎች ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምረው በሕዝቡ ላይ የተለያዩ ታርጋዎች በመስጠት እና ስሁት ትርክት በመፍጠር ጎድተውታል ነው ያሉት።
ከኢትዮጵያውያን አህት ወንድሞቹ ጋር አብሮ እና ተባብሮ አንዳይሠራ ብሎም አንዳይኖር አዛኝ እና ተቆርቋሪ በመምሰል በውስጥ ባንዳዎች ተላላኪነት ብዙ ተንኮል እና ሴራ አየተሠራበት መቆየቱንም ተናግረዋል። የክልሉ ሕዝብ ሙሉ አቅሙን በሰላም እና ልማት ሥራ ላይ አዳያውል አድርገውታል፤ አያደረጉትም ነው ብለዋል።
የእስካሁኑ በደሉ አልበቃ ብሎት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከዓለም እንዲነጠል እና የቁም ሞት አንዲሞት በማሰብ ልጆቹን አንዳያስተምር አየተደረገ ነው ብለዋል። አናስተምር ያሉ መምህራን ተገድለዋል፤ ተንበርክከው ተገርፈዋል፤ ታግተዋል፤ ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል፤ ወንበሮች ተማግደዋል፤ መጻሕፍት ተቃጥለዋል፤ በጥቅሉ የትውልድ ቅብብሎሹ አንዲቋረጥ የሚያደርጉ ተግባራት እየፈጸሙ ነው ብለዋል።
በ2016 ዓ.ም በዓመቱ መጀመሪያ ተመዝግበው ትምህርት ይማራሉ ተብለው ከታቀዱት 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ ተመዝግበው ትምህርት የጀመሩት 58 በመቶ ብቻ እንደነበሩ ያስታወሱት ኀላፊዋ 42 በመቶ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ከርመዋል ነው ያሉት። 4 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው መክረማቸውንም አስታውሰዋል። በ2017 የትምህርት ዘመንም 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስካሁን ድረስ የተመዘገቡት 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸው ብለዋል።
የተዘመገቡት ተማሪዎችም 40 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ይህ ማለት ከጥቂት ዓመታት በኋላ የክልሉ ሕዝብ የሚያፈራው ምሁር አይኖርም ማለት ነው ብለዋል። በዚህ ከቀጠልን ሕዝብ ከዓለም ሁለንተናዊ የጉዞ መስመር ይወጣል ነው ያሉት። አሁን ከገጠመን ችግር ልንወጣ ከኾነ መፍትሔው ችግሩ ዘመን ተሻጋሪ መኾኑን አውቀን፤ ትክክለኛ ጠላታችንን እና በደሎቹን ተረድተን ተባብረን ወደ መፍትሔው ጎዳና ፊታችንን ማዞር ነው ብለዋል።
ሰላም ለትምህርት፤ ትምህርት ለሰላም ያላቸውን ቁርኝት አውቀን የባከነውን ጊዜ በሚያካክስ መልኩ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ባለፉት ጊዜያት የውይይት መድረኮች እና በሦስት ዙር የተማሪዎች ምዝገባ መካሄዱንም ተናግረዋል። በትምህርት የገጠመን ችግር ውስብስብ ነው ብለዋል። ከችግሩ ለመውጣት ትምህርትን የኅብረተሰቡ አጀንዳ ማድረግ ወሳኝ መኾኑንም አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!