
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ዳፋውን አሳርፏል። የክልሉ መንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚኾኑ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ አድርጓቸዋል።
በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን በተደረገው ጥረት ሰላማቸውን ጠብቀው በሚገኙ አካባቢዎች ደግሞ የመማር ማስተማር ሥራው በተሻለ መንገድ እየተሰጠ ይገኛል። በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ አሥተዳደር የተሻለ ሰላም በመኖሩ የመማር ማስተማር ሥራው ያለመቆራረጥ እየተከናወነ መኾኑን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።
መማር ማስተማሩ ከተጀመረበት ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ቤቱ፣ በመምህራን እና በወላጆች እገዛ ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ መኾናቸውን የደባርቅ ሁለተኛ እና መሠናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናግረዋል። ሰላም ባይኾን ትምህርት ቤት አንገኝም ነበር ያሉት ተማሪዎቹ በዚህ ጊዜ ትምህርት መከታተላችን እድለኛ ያደርገናል ነው ያሉት።
በከተማ አሥተዳደሩ የትምህርት ሥራ የተጀመረው በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መርሐ ግብር መሠረት ነው ያሉት የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈረደ ይትባረክ በከተማው በጥቅሉ ከ18 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ከዚህ ቀደም በተማሪዎች ላይ ይታይ የነበረውን የጥራት፣ የመድገም፣ የማቋረጥ እና መሰል ችግሮች ለመፍታት ከመደበኛ መማር ማስተማሩ ጎን ለጎን እሁድ እና ቅዳሜን ጨምሮ ተማሪዎችን የመደገፍ ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑ ኀላፊው አብራርተዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ አጸደ በሬ በዞኑ ከሚገኙ 490 የትምህርት ተቋማት ውስጥ 125 ትምህርት ቤቶች በጸጥታ ችግሩ ከመማር ማስተማር ውጭ ኾነው እንደሚገኙ ተናግረዋል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ከ110 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ወይዘሮ አጸደ በትምህርት ዘመኑ ከተመዘገቡት 174 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል 149 ሺህ በላይ የሚኾኑት አሁን ላይ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መኾናቸውን አንስተዋል። ከመማር ማስተማር ውጭ የኾኑ ተማሪዎችን ለመመለስ በንቅናቄ በተሠራው ሥራ ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እና በዳባት ወረዳ የሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶችን ወደ መማር ማስተማር ሥራው እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል።
ሰላም ባለባቸው የዞኑ አካባቢዎች መጻሕፍትን በአግባቡ በማዳረስ የተሻለ መማር ማስተማር እንዲኖር፣ ክልል አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችም ውጤታማ እንዲኾኑ የመደገፍ ሥራም እየተከናወነ እንደሚገኝም ምክትል ኀላፊዋ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን