
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የትምህርት ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው። በንቅናቄ መድረኩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በንቅናቄ መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ትምህርት ቤቶች ለልጆቻችን አመች፤ ዕውቀት መቀበል የሚችሉ ደስተኛ ልጆች ለማፍራት የሚያስችሉ እንዲኾኑ በመላው ሀገሪቱ እየሠራን ነው ብለዋል።
በተለያዩ ክልሎች የተነሱ ግጭቶች በትምህርት ዘርፉ እያደረግን ያለነውን የለውጥ ሂደት ከፉኛ እየተፈታተኑት ነው ያሉት ሚኒስትሩ ግጭቶቹ በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች ያሉትንም ሕጻናት እና ወጣቶች በትምህርት ሊያገኙት የሚችለውን የወደፊት ዕድል ክፉኛ ሲያጨናግፉት እናያለን ነው ያሉት።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት እና የግጭቱ ጦስ በነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናት እና ወጣቶች ላይ ያመጣውን እና እያስከተለው ያለውን የሥነ ልቦና ጠባሳ ሳይ ከፍተኛ ቁጭት እና ሀዘን ይሰማኛል ብለዋል።
እንደ ሀገር “ትምህርት ለትውልድ” የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ ባለፉት ጊዜያት ከ39 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ሕዝቡ አሠባሥቧል ነው ያሉት። በዚህም 5 ሺህ 957 ቅድመ አንደኛ፣ 1 ሺህ 738 የአንደኛ እና መካከለኛ፣ 268 የሁለተኛ ደረጃ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል ብለዋል።
31 ሺህ 252 ትምህርት ቤቶች ጥገና እና እድሳት ተደርጎላቸው የመማር ማስተማር ሥራውን እንዲያከናውኑ መደረጉንም አንስተዋል። በግጭት ውስጥም ኾኖ በአማራ ክልል ብቻ የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሠባሠብ አዳዲስ የትምህርት ቤቶች ግንባታ እና የነባር ትምህርት ቤቶች ጥገና ተከናውኗል ብለዋል።
በንቅናቄው በመላ ሀገሪቱ ኅብረተሰቡ ልጆቹን ለማስተማር ያለውን ፍላጎት እና ከፍተኛ ትጋት ማየታቸውንም ተናግረዋል። ግጭቶች በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች የትምህርት ሥርዓቱ ክፉኛ ከሚጠቁ ዘርፎች አንዱ መኾኑንም አንስተዋል። ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉ ሕጻናት በብዙ መልኩ ከማንም በላይ ተጎጂ ናቸው ነው ያሉት።
“ትምህርት ቅንጦት ሳይኾን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ነው” ያሉት ፕሮፌሰሩ ሕጻናት ወደፊት ዕጣፈንታቸውን የሚገነቡበት፣ ችሎታቸውን የሚከፍቱበት ቁልፍ መሳሪያ እና ድልድይ ነው ብለዋል። ነገር ግን በብዙ የዓለም ክፍሎች የሚካሄድ ግጭት እና ጦርነት ይህን መብት እየጣሰ ነው ብለዋል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች እና ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውንም አንሰተዋል። የትጥቅ ግጭት የሚያስከትለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፣ ትምህርት ቤቶች ይወድማሉ፤ መምህራን ይፈናቀላሉ፣ ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው ይለቃሉ፣ በብዙ ዘመን እና ድካም የተገነባውን የኅብረተሰቡን መዋቅር የሚያፈርስ እና የሕጻናት እና ወጣቶችን ብሩህ የወደፊት ተስፋ የሚሸረሽር ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ግጭት ብሎም ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ በተከሰተባቸው ከልሎች በርካታ ሕጻናት እና ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል ነው ያሉት። በዚህ ዓመት እንደ ሀገር ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ከነበረባቸው ውስጥ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል።
በአማራ ክልል ብቻ አሁን ባለው ግጭት ምክንያት ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል ነው ያሉት። ከ3 ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ሥራው ውጭ ኾነዋል ነው ያሉት። የዚህን ክፉ ተግባር ውጤት ምንነት ከዛሬም በላይ ገና ወደፊት ይገለጣል ብለዋል።
የግጭቱ ሰለባ የኾኑ ተማሪዎች ላይ የሥነ ልቦ ጫና እየደረሰባቸው እና የተማሪዎች የወደፊት የሕይወት ዕድል እየተሰናከለ መኾኑንም ገልጸዋል። የአማራ ከልል ልጆች እና ወጣቶች በሌሎች ክልሎች ካሉ እኩዮቻቸውም ይሁን ሰላም ባለባቸው አካባቢ ካሉ ልጆች አንጻር ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰባቸው መገንዘብ ይቻላል ነው ያሉት።
ትምህርት የረጅም ጊዜ ሥራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ትምህርት በአንድ ዓመት እና በሁለት ዓመት ሲቋረጥ የሚፈጠረው የሥነ ልቦና ጫና እጅግ ከባድ ነው ብለዋል። እነዚህ ልጆች ወደ ትምህርታቸው ተመልሰው ቢገቡም እንኳን የደረሰባቸው የሥነ ልቦና ቀውስ ትምህርት የመቀበል አቅማቸውን እንደሚጎዳው ነው የተናገሩት። በተጨማሪም በግጭት ጊዜ ያለፈውን ትምህርት ለማካካስ አስቸጋሪ ይኾናል ብለዋል።
እንደምንም አካክሰው እንኳን ትምህርታችውን ቢቀጥሉ በዕድሜ ከነሱ ካነሱ እና ከታናናሾቻቸው ጋር መማራቸው ጫናውን የጎላ ያደርገዋል ነው ያሉት። ግጭት የልጆቻችንን የወደፊት ዕድል ክፉኛ እንዳያበላሽ መጠንቀቅ፤ በግጭቶች አካባቢ ያሉ ትምህርት ቤቶች ዓለማቀፍ ሕግጋት እንደሚያዙት ከማንኛውም ወገን ጥቃት እንዳይደርስባቸው እና ልጆች ትምህርታቸው እንዳይሰናከልባቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል። ይሄን ለማድረግ የወላጆች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ሚና ከፍተኛ መኾኑንም አመላክተዋል።
የሰው ልጅ በጥላቻ እና በፉክክር ሲዋጥ ከምክንያት እና ከንግግር ሲርቅ የሚፈጥራቸው ግጭቶች ሊያደርሱ የሚችሉትን ውድመቶችም አይተናል ነው ያሉት። ትምህርት ቤቶች ልጆችን ምክንያታዊነትን፤ ግብረገብነትን እና ከህሎቶችን እንዲጨብጡ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። የማይኾን ፍክክር እና ውድድር በስሜት ብሎም በጥላቻ ውስጥ መኖር የዛሬውን ሕይወት ብቻ ሳይኾን የመጭውንም ይጎዳል ብለዋል።
እንዲህ በተደበላለቀ ጊዜ ውስጥ ያሉ ዜጎች እጣ ፈንታቸው መተሳሰር እና መተባበር መኾኑን አውቀው በጋራ መቆም ይገባቸዋል ብለዋል። እርስ በእርስ ባላቸው ተጓዳኝ ልዩነት መናናቅ፣ በጎጠኝነት፣ በጠባብ በማሰብ አካባቢያቸውን ከውጭ ለሚመጡ አደጋዎች ማጋለጥ አይገባቸውም ነው ያሉት።
የኮሎኒያሊዝም መስፋፋት ምክንያቶች በቅኝ ተገዥ ሀገራት ያሉ ልዩነቶች መኾኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ዛሬ ላይ ቆመን ከታሪክ አለመማር ይቅር የማይባል አላዋቂነት ነው ብለዋል። ከግጭት ይልቅ ሰላምን ፣ ከማይኾን ፉክክር ይልቅ መተባበር እና መተጋገዝን ማስቀደም ይገባል ነው ያሉት። የ21ኛውን ከፍለ ዘመን ተግዳሮቶች ቀድሞ ማወቅ እና መቋቋም የሚችሉ ወጣቶችን ለማፍራት መዘጋጀት ይኖርብናል ነው ያሉት።
የትምህርት ሥርዓታችን ከፍተኛ የኾነ የጥራት ችግር ያለበት እና በትውልዱ መካከል የሞራል ውድቀትን ያስከተለ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ ይህንን ከመሠረቱ ለማስተካከል በትምህርት ዘርፉ ግልጽ ራዕይ በማስቀመጥ ፍትሐዊ እና ጥራት ያለው ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የለውጥ ተግባራትን ቀርጸን ተግባራዊ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
በተለይም የሥርዓተ ትምህርታችን ከ21 መቶ ክፍለ ዘመን ፍላጎቶች ጋር የሚዛመድ እንዲኾን በማድረግ ወደ ሙሉ ትግበራ ገብተናል ነው ያሉት። ይህንን ራዕይ ለማሳካት አንድ ላይ ኾነን ከተባበርን የትምህርት ሥርዓቱን ውጤታማ ማድረግ እንችላለን ብለዋል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኝ በማድረግ ብቁ እና ብቃት ያላቸው፣ ሥነ ምግባር የተላበሱ ትውልዶችን ማፍራት እንችላለን ነው ያሉት።
ትምህርት መንግሥትን ብቻ ሳይኾን ወላጆችን፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ እና የአካባቢውን ድርጅቶች የሚያሳትፍ የጋራ ጥረት የሚፈልግ ነው ብለዋል። ወላጆች እና የማኅበረሰብ አባላትን በትምህርት ሂደት ውስጥ በባለቤትነት በማሳተፍ የተማሪን የመማር ስኬት የሚያጎለብቱ ድጋፎችን እንዲያደርጉ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን በመላው ሀገሪቱ ለማሻሻል እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ሁሉንም የሀገሪቱን ልጆች በእኩልነት በማየት፤ በግጭት ውስጥ ላሉ እና በዚያ ላለፉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተለየ አትኩሮት በመስጠት፣ በግጭት የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ በመገንባት፤ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች እንደ ፍላጎቱ መጠን እና በመስሪያ ቤቱ አቅም ልክ እያገዘ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል በጦርነት የፈረሱ 45 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ገንብተን አስረከበናል ነው ያሉት። በዚህ ዓመት ሁለተኛ ደረጃ ትምህትት ቤቶች ላይ በማተኮር 17 ትምህርት ቤቶችን በአማራ ከልል ለመገንባት ተዘጋጅተናል ብለዋል። የሁሉንም ትምህርት ቤቶች ግንባታ ክረምት ከመግባቱ በፊት እናስጀምራለን ነው ያሉት። አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቀቁም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ከግጭት ወጥቶ፤ ከትምህርት ገበታ የራቁትን ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤቶች ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት ትምህርት ሚኒስቴር በተቻለው አቅም ሁሉ እንደሚተባበርም አስታውቀዋል። “ትምህርት ለትውልድ” የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ የተሳካ እንዲኾን በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች፣ የቀድሞ ተማሪዎች፤ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች፣ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ የልማት ድርጅቶች በትውልድ ቦታቸው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!