
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአማራ ክልል የትምህርት ንቅናቄ ላይ ለመሳተፍ ባሕር ዳር ከተማ ገብተዋል።
ሚኒስትሩ ባሕር ዳር ከተማ ሲገቡ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በተጨማሪ የትምህርት ሚኒስትር ዴዔታ አየለች እሸቴን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል የሥራ ኀላፊዎች ዛሬ በሚጀመረው ክልላዊ የትምህርት ንቅናቄ ለመሳተፍ ባሕር ዳር ገብተዋል።
በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የክልሉ ትምህርት ተጎድቷል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አልተመለሱም። ይሄም የትውልድ ክፍተት እንዳይፈጠር ስጋት ኾኗል።
ዛሬ የሚካሄደው የትምህርት ንቅናቄ በትምህርት ዘርፉ በደረሰው ጉዳት ላይ በመምከር የቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!