
👉 አርበኛ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር!
ባሕር ዳር: መጋቢት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደጃዝማች ዑመር ሰመተር በ1880 ዓ.ም በኦጋዴን አካባቢ ካልካዩ በተባለ ሥፍራ ተወለዱ።
የመጀመሪያ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ኤደን ተጉዘው ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ቁርዓን በማስተማር ላይ ሳሉ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ለሀገራቸው ነጻነት ተነሱ።
በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት በምሥራቃዊ ኢትዮጵያ ከደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት እና ከሌሎች አርበኞች ጋር በመኾን ተዋግተዋል። ወልወል ላይ ጣሊያን የጫረችውን ግጭት ተከትሎ በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረውን ተቃውሞ በመምራት የላቀ ሚና ተጫውተዋል።
በተለያዩ የጦር ግንባሮች ላይ የላቀ ጀብዱ በመፈፀም የጣሊያንን ጦር ድባቅ መተዋል። በተለይም በገርለጉቤ፣ በኤልቡር፣ በሺላቦ እና በቆራሄ አካባቢዎች ያደረጓቸው ጦርነቶች የጀግንነታቸው ማሳያዎች ናቸው።
በኤልቡር በስድስት የጣሊያን ጦሮች ሲከበቡ በጀግንነት ምሽጉን ሰብረው በመውጣት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ወስደዋል። የአካባቢውን ሕዝብ በማስተባበር እና በማደራጀት ለሀገራዊው ተጋድሎ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
በጀግንነታቸው የፊታውራሪነት ማዕረግ ተሰጧቸዋል። በአዲስ አበባ የሚገኘው እፎይታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በደጃዝማች ኡመር ሰመተር ስምም እንዲሰየም ተደረገ።
ጀግናው አርበኛ በዚህ ሳምንት መጋቢት 10 ቀን 1936 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ሥርዓተ ቀብራቸው በሀረር ከተማ ተፈጽሟል።
👉ዶክተር ካትሪን ሐምሊን!
በኢትዮጵያ የፊስቱላ ተጠቂዎችን ሕይወት በመለወጥ የሚታወቁት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ከ60 ዓመታት በላይ በዚህ ዓላማ ሲያገለግሉ ኖረዋል።
ዶክተር ካትሪን ሐምሊን እና ባለቤታቸው ዶክተር ሄግ፣ የጽንስና ማኅፀን ሕክምና ስፔሻሊስቶች ነበሩ። በ1959 እ.ኤ.አ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በወሊድ ምክንያት በሚከሰት የፊስቱላ ሕመም የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያንን ከፍተኛ የጤና ችግር ለመቅረፍ ሰርተዋል።
በአዲስ አበባ “ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል” የተሰኘ ተቋም መሠረቱ። ዛሬ ላይ ሆስፒታሉ ከአዲስ አበባ ውጭ ቅርንጫፎችን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው።
ባለቤታቸው ዶክተር ሄግ ቀደም ብሎ ሕይወታቸው ቢያልፍም፣ ዶክተር ካትሪን ሐምሊን እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያን እናቶችን አገልግለዋል።
ዶክተር ሐምሊን “ደስታ መንደር” የተሰኘ ማገገሚያ ማዕከልን በማቋቋም ይታወቃሉ። ይህ ማዕከል የፊስቱላ ሕመም ያለባቸው ሴቶች ጊዜያዊ ወይም ዘለቄታዊ የሕክምና ክትትል የሚያገኙበት እና ደስተኛ ሕይወት እንዲመሩ የሚረዳ ነው።
በየዓመቱ የፊስቱላ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ መንግሥት ከአዲስ አበባ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ገፈርሳ መኖ ቀበሌ 60 ሄክታር መሬት በመስጠት የደስታ መንደር ተመሥርቷል።
የኢትዮጵያውያን እናቶች ባለውለታ የኾኑት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በ96 ዓመታቸው አርፈዋል።
ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በኢትዮጵያ ላከናወኗቸው መልካም ተግባራት የመንግሥት የክብር ዜግነት እንዲኹም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል።
👉ዓለም አቀፉ የደን ቀን!
ዓለም አቀፉ የደን ቀን በየዓመቱ መጋቢት 12 ቀን የሚከበር ሲኾን፣ ስለ ደኖች ያለንን ግንዛቤ ለማሳደግ እና የደን ጥበቃን ለማበረታታት ዓላማ ያደረገ ነው።
ይህ ቀን በዚህ ሳምንት እንደ እ.ኤ.አ በ2012 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ የተቋቋመ ነው። በዓሉም ደኖች ለሰው ልጆች እና ለምድራችን ያላቸውን ጠቀሜታ ለማጉላት ያለመ ነበር።
የዓለም አቀፉ የደን ቀን ዋና ዓላማውም የደን ጥበቃን አስፈላጊነት ለማስተማር፤ የደን ብዝኃ ሕይወትን ለመጠበቅ፣ የደን ዘላቂ አጠቃቀምን ለማበረታታት፣ የደን ውድመትን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ያለመ ነው።
ዓለም አቀፉ የደን ቀን ስለ ደኖች ግንዛቤ ለማሳደግ እና የደን ጥበቃን ለማበረታታት ትልቅ ዕድል እንዳለውም ከተመድ የተገኘው መረጃ የሚያሳየው።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!