
ባሕር ዳር: መጋቢት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የፖለቲካ እና የድርጅት ሥራዎች የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው።
በግምገማው ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙ ሥራዎች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ቀርበዋል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ባለፉት ስምንት ወራት ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው ተግባራት መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡
ውጤታማ የመስኖ ልማት እና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች መሥራታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በመስኖ ልማት 96 በመቶ ዕቅዳችንን አከናውነናል ነው ያሉት፡፡
ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት መቻሉንም ገልጸዋል፡፡ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ደግሞ በደጋፊ መስኖ ቀሪ ሥራዎችን እንፈጽማለን ብለን እንጠብቃለን ነው ያሉት፡፡
በተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራም መልካም ተግባራት ተሠርቷል ያሉት ኀላፊው በክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ባለፈው ዓመት ችግር ገጥሞት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ዓመት ግን ባለፈው ዓመት የታጣውን ዕድል ሁሉ ማካካስ የሚያስችል ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት አድርገናል ነው ያሉት፡፡ 82 በመቶ የሚኾነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ መሠራቱንም አስታውቀዋል፡፡ መቶ በመቶ ሳናሳካ ሥራውን አናቋርጥም በሚል ቁርጠኝነት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
በውይይቱ እየተሳተፉ ያሉ መሪዎችም ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ እና የግብርናውን ዘርፍ እንዲያነቃንቁ የሚያስችል ውይይት አድርገናል፤ አቅጣጫም አስቀምጠናል ነው ያሉት፡፡
ግብርና ቢሮ በትኩረት እየተሠራ ያለው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ነው ያሉት ኀላፊው ለአማራ ክልል 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል ብለዋል፡፡ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ ወደ ክልሉ ገብቷል ብለዋል። ወደ ክልሉ የገባው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሠራጨ መኾኑንም ዶክተር ድረስ ተናግረዋል፡፡
ለመኸር እርሻ የአፈር የማዳበሪያ እጥረት እንዳይገጥም ሠፊ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ለመስኖ ልማት ሥራው በቂ ማዳበሪያ ማቅረባቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የግብርና ምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ለመጠቀም መንግሥት ልዩ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የግብዓት አቅርቦቱ ያልተገባ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳይኾን ከአርሶ አደሮች ጋር በመወያየት መግባባት ላይ ደርሰናል ነው ያሉት፡፡ መንግሥት ለማዳበሪያ ድጎማ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት፣ የዘር አቅርቦት እና ሥርጭትም በጥሩ ሂደት ላይ ነው ብለዋል፡፡ ከግብርናው ባሻገር በገጠር ኢኮኖሚ ዘርፍ የሚገኙ ተቋማትን ሥራም መገምገማቸውን አንስተዋል፡፡
ግብርና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሰብሎችን በስፋት ማምረት እና ማቅረብ፣ ከውጭ የሚገቡትን በሀገር ውስጥ መተካት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚኾኑ ምርቶችን ማምረት እና የምግብ ዋስትናን በራስ አቅም ማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በተሠሩ ሥራዎችም ጥሩ ውጤቶች መገኘቱን ነው የተናገሩት፡፡
ክልሉ ከፍተኛ የኾነ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረቡንም ተናግረዋል፡፡ ይህም በምርት ጭማሪ ላይ የታየውን ለውጥ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ ክልሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሰብሎችን በማምረት ከፍተኛ ሥራ እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
አማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ብዙ ፈተናዎችን አሳልፏል ያሉት ኀላፊው ማኅበረሰቡም ከፈተናዎቹ ብዙ ትምህርት ያገኘ ይመስለኛል ነው ያሉት፡፡ ችግሮችን በሠለጠ መንገድ በመፍታት ፊትን ወደ ልማት ማዞር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ችግሮችን በኃይል እፈታለሁ የሚል እሳቤ የክልሉን ሕዝብ ጎድቶታል ብለዋል፡፡ በኃይል የሚፈታ ችግር፣ የሚመለስ ጥያቄ የለም ያሉት ኀላፊው ብቸኛው አማራጭ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ በሰላም መፍታት መኾኑን ነው ያነሱት፡፡
ኅብረተሰቡ አፍራሽ የኾነን የጽንፈኝነት አስተሳሰብ መታገል እና እረፉ ማለት አለበት ብለዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት የትግል ስልት የሚመጣ አንድነት፣ የሚመለስ የኢኮኖሚ ጥያቄ የለም፣ የሚሻለው መነጋገር ነው፤ መላ ኅብረተሰቡ ለሰላሙ ዘብ ሊቆም ይገባል፤ መንግሥት የሚያደርገውን የሕግ ማስከበር ሥራ መደገፍ አለበት፤ ለሀገር ዕድገት እና ለሕዝብ አንድነት የማይጠቅሙ እሳቤዎችን አምርሮ መታገል አለበት ነው ያሉት፡፡ ሀገር የሁሉም እንደኾነች ሁሉ፣ ሰላሟም የሚረጋገጠው በሁሉም ተሳትፎ ነው ብለዋል። ቢያንስ በጋራ ጥቅሞቻችን እና በጋራ ጉዳዮቻችን በልዩነት መቆም የለብንም ነው ያሉት፡፡
በሀገር ሰላም፣ በሀገር አንድነት፣ በሕዝብ ጥቅም ላይ የሚመጡ ጉዳዮችን በትኩረት መመልከት፣ ሰላምን ማስቀደም ይገባል ብለዋል፡፡ ሀገር የሚገነባው በንግግር እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ሲመለሱ ሌሎች ጥያቄዎችም አብረው ይመለሳሉ ነው ያሉት፡፡ “ሙሉ ትኩረታችን በጸረ ድህነት ትግል ላይ መኾን አለበት” ብለዋል፡፡
በኢኮኖሚ የጠነከረች ሀገር የሚገነባው በጸረ ድህነት ትግል ላይ ትኩረት ሲደረግ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ እርስ በእርስ በመዋጋት የሚበለጽግ ሀገር የለም ነው ያሉት፡፡
ባለፈው ዓመት የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በመውሰድ ምርት እና ምርታመነትን ለማሳደግ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል፡፡ የማዳበሪያ አቅርቦቱ ዕቅድ ከአምናው የበለጠ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት የክልሉን የምርጥ ዘር ፍላጎት ሸፍነን ለሌሎች ክልሎች መስጠት የሚያስችል አቅም ፈጥረናል ነው ያሉት፡፡
በተለይም በበቆሎ ምርጥ ዘር ላይ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ በባለፈው ዓመት የነበረው የማዳበሪያ አቅርቦት እና ሥርጭት ስኬታማ ነበር ያሉት ኀላፊው ዘንድሮም በጥሩ ሁኔታ ለመፈጸም በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ዓመት የተገኘው የማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት ስኬት በቅንጅት የመጣ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ዘንድሮም ቅንጅቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡ የጸጥታ ኃይሉ የማዳበሪያ ሥርጭቱን በስኬት እየተወጣ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን ያለው ስርጭትም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው፣ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!