
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሠራዊቱን አቅም የማሳደግና ፕሮፌሽናል ሠራዊት የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ።
በመከላከያ ትምህርት እና ሥልጠና መምሪያ የአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት ያሠለጠናቸውን የሜካናይዝድ ሙያተኞች አስመርቋል።
በመርሃ ግብሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ የመከላከያ የመረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጀነራል ጌታቸው ጉዲና፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ዓለምሸት ደግፌ፣ የመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን፣ የሜካናይዝድ እዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አምዴ እንዲሁም ሌሎች የሠራዊቱ አመራሮች እና አባላት ተገኝተዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ሀፍረት እያከናነበች ያለች ሀገር ናት ብለዋል።
አሁንም ሰላሟን ለመንሳት የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ባንዳዎችም ኢትዮጵያ ወደ ፊት እንዳትራመድ የቻሉትን ሁሉ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ሠራዊቱ እንደወትሮው ሀፍረት እያከናነባቸው ይገኛል ብለዋል።
ሰራዊቱ በስትራቴጂው በመመራት በባሕር፣ በምድር፣ በአየር እንዲሁም በሳይበር ከፍተኛ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የሜካናይዝድ ኃይል አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ኃይል የሠራዊቱ ቀኝ እጅ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የሠራዊቱን አቅም የማሳደግ እና ፕሮፌሽናል ሠራዊት የመገንባቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
ሠልጣኞች ባገኙት እውቀት በመታገዝ ኢትዮጵያ የያዘቻቸው አላማዎች እንዲሳኩ ዘወትር እንዲተጉም አሳስበዋል።
የሜካናይዝድ እዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አምዴ በበኩላቸው ለሜካናይዝድ ኃይል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ግልጽ ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተተገበረ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ስትራቴጂው ጠንካራ ለሀገር አለኝታ እና መከታ የሆነ የሜካናይዝድ ኃይል ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንና የተሻለ ሥራ ለመሥራት ምቹ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!