
ባሕር ዳር: መጋቢት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራችን ምልክት የኾኑትን ዋልያዎች ቁጥር መቀነሱ አሳሳቢ መኾኑን በመገንዘብ የመንከባከብ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የአፍሪካ ጣሪያነት ተፈጥሮ የቸረችው ማዕረጉ ነው። የተራራዎች አውራ የኾነው ራስ ዳሽን ተራራ በክብር የቆመው በዚሁ ፓርክ ውስጥ ነው። የሀገር ምልክት የኾነው ዋሊያም ከሀገር ኢትዮጵያን፣ ከተራራዎች ደግሞ ራስ ዳሽንን ብቻ ነው መርጦ ቤት ያደረገው።
ለዐይን የሚማርኩ ሰንሰለታማ ተራራዎች፣ ብርቅየ የዱር እንስሳት፣ እንደ ጅብራ ያሉ በርካታ ሀገር በቀል እጽዋት፣ እና ውብ የኾኑ አካባቢያዊ ባሕል እና እሴቶች ሁሉ ታይተው የማይጠገቡ የፓርኩ ገጸ በረከቶች ናቸው።
ፓርኩ ለሀገር የሚተርፍ የቱሪዝም ጸጋ ያለው አንጡራ ሀብት ነው። በጸጋው ልክ የሚኾን ተጨማሪ ሀብት ያመነጭ ዘንድ መጠበቅ፣ መንከባከብ እና ማልማት ግድ ይላል።
በዛሬው የአሚኮ ቱሪዝም ዝግጅታችንም የዚህ ፓርክ የበጋ የእንክብካቤ፣ የእንስሳት ጥበቃ እና የልማት ሥራዎችን የምንዳስስ ይኾናል።
የፓርኩ ጽሕፈት ቤት የሥነ ምኅዳር ክትትል እና ማበልጸግ የሥራ ክፍል ኀላፊ ኤፍሬም ወንዴ እንደሚሉት በየዓመቱ ከጥር ወር ጀምሮ እስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ ፓርኩ የእሳት አደጋ ስጋት አለበት። አደጋው በገቢር ተከስቶም ጉዳት ያደረሰባቸው ዓመታት ይታወሳሉ።
ይህ የእሳት አደጋ እንዳይነሳ ቀድሞ መከላከል ይቻል ዘንድ በፓርኩ ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎችን በእሳት መከላከል ግብረ ኃይል በማሠልጠን አሰማርተናል ነው ያሉት። ለወትሮው ያሰጋ የነበረውን የቃጠሎ ስጋት ቀንሷል፤ በዚህ ዓመት የተከሰተ ቃጠሎም የለም ብለዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ፓርኩን “የኔ” ብሎ እንዲጠብቀው የሚያስችል የተጠቃሚነት አሠራር ስለመዘርጋቱም ኀላፊው ተናግረዋል። ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ጎብኝዎች አገልግሎት የሚሰጡ የማኅበረሰብ ሎጅዎችን በመገንባት ነዋሪዎች እንዲያስተዳድሯቸው እና ጥቅም እንዲያገኙባቸው እየተደረገ መኾኑን አብራርተዋል። የጋማ ከብቶችን በማከራየት እና የተለያዩ የቱሪስት አገልግሎቶችን በመስጠት የተደራጁ ማኅበራትንም ጥቅም እያገኙ ነው ብለዋል።
ይህ ተጠቃሚነት ፓርኩን በባለቤትነት ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ እና ለማልማት ሁነኛ መንገድ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
አቶ ኤፍሬም እንዳሉት ብርቅየ እንስሳትን የመንከባከብ እና ቁጥራቸውን ለመጨመርም በትኩረት እየተሠራ ነው። በተለይም የዋልያዎች ቁጥር በመቀነሱ ልዩ እንክብካቤ እና ክትትል አስፈልጓል ነው ያሉት። ይህንን ቁጥር ለማሳደግ በሀገር አቀፍ ደረጃም ልዩ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የፓርኩን አረንጓዴ መልክ ለመጠበቅ ሲባል በክረምቱ ወራት የተተከሉ ችግኞች በበጋው ወራት እንዳይደርቁ እንክብካቤ እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማሩ ቢያድግልኝ በበጋ ወቅት በፓርኩ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል እየተሠራ ነው ብለዋል። የተቋቋመው የእሳት መከላከል ግብረ ኀይል የነበረውን ስጋት በመቀነስ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱንም ገልጸዋል።
በፓርኩ ዙሪያ ልቅ ግጦሽ እንዳይኖር፣ ሕገ ወጥ ዛፍ ቆረጣ እንዳይካሄድ፣ ሳር አጨዳ እንዳይከናወን እና ያለማወቅ የሚፈጸሙ የተለያዩ ፓርኩን የሚጎዱ ድርጊቶች ከመከላከል አኳያም በየቦታው የሰው ኀይል ተመድቦ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የእንስሳት ብዝኃ ሕይወትን ለመንከባከብ እንዲያመች በየዓመቱ ሁለት ጊዜ ቆጠራ እንደሚካሄድ የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ተናግረዋል። የዋሊያዎች ቁጥር ቀደም ሲል 1 ሺህ ይደርስ ነበር፤ በዚህ ዓመት ቆጠራ ግን 306 መድረሳቸው ታውቋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ምልክት የኾኑትን የዋሊያዎች ቁጥር ለመጨመር እንደትልቅ የቤት ሥራ ተወስዶ እየተሠራ ነው ብለዋል። የቀነሰውን የዋልያዎችን ቁጥር መልሶ የመጨመር ብሔራዊ ዕቅድ ወጥቶ እየተገመገመ ነው፣ በቀጣይም ወደ ተግባር ወርዶ ይሠራበታል ነው ያሉት።
የቀይ ቀበሮዎች ቁጥር ከሰባ በላይ እንደሚኾን እና አዳዲስ ግልገል ቀይ ቀበሮዎች እየታዩ እንደኾነም ገልጸዋል።
ጽሕፈት ቤቱ ከእንስሳት ቆጠራ፣ ክትትል እና እንክብካቤ በተጨማሪ ባለሙያዎችን መድቦ እያሠራ መኾኑንም አቶ ማሩ ተናግረዋል። ይህም የእንስሳት ብዝኃ ሕይወትን ለመከታተል እና ቁጥራቸውን ለማሳደግ ያስችላል ነው ያሉት።
ቱሪዝም ሰላምን ይፈልጋል ያሉት የጽሕፈት ቤት ኀላፊው ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር እንቅፉት ፈጥሮ እንደነበር ጠቁመዋል። ያም ኾኑ በበጀት ዓመቱ እስካሁን ድረስ 2 ሺህ 500 የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ፓርኩን ጎብኝተዋል። በተለይም ጥምቀት እና ገናን ተንተርሰው አሁንም ደረስ ከ20 እስከ 30 እየኾኑ በቡድን የሚጎበኙ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች አሉ ብለዋል አቶ ማሩ።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!