ምዝገባው ለተማሪዎች ተጨማሪ ዕድሎችን ፈጥሯል።

26

ባሕር ዳር: መጋቢት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክቴ አያሌው በሰሜን ጎጃም ዞን የቅንባባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ናት።

እንደ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት እስከ ጥር ወር መጨረሻ 2017 ዓ.ም ድረስ ትምህርት ቤታቸው ባለመከፈቱ መቆጨቷን ተናግራለች።

ትምህርት ቤት በመዘጋቱም አንዳንድ ጓደኞቿ መዳራቸውን፣ ሌሎቹ ወደ ሌላ ሥፍራ መሄዳቸውን ስትሰማ በ”ነግ በኔ” ሥጋት ላይ ወድቃ እንደነበር ተማሪ የክቴ አስታውሳለች።

ከወራት የደበዘዘ ተስፋ በኋላም በአካባቢያቸው ሰላም ሰፍኖ ትምህርት ቤት በመከፈቱ እሷ እና ጓደኞቿ የመማር ዕድሉን አግኝተው የጨለመው ተስፋቸው በመገለጡ መደሰቷን አልሸሸገችም።

በዳንግላ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አቶ ከበደ የኔው እንዳሉት በጸጥታ ችግር የተነሳ ትምህርት ቤት ተዘግቶ በመቆየቱ አካል ጉዳተኛ የኾነው ልጃቸው በሥነ ልቦና ተጎድቷል። ይሁንና በቅርቡ ትምህርት በመጀመሩ የልጃቸው ዶክተር የመኾን ተስፋው መልሶ ፈንጥቋል።

አቶ ከበደ አያይዘውም ልጃቸው ያገኘውን መልካም አጋጣሚ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎችም የዕድሉ ተጠቀሚ እንደሚኾኑ ተስፋ አሳድረዋል።

በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ቅንባባ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቋንቋ መምህር ፀጋዬ ገሠሠ ቀድመው ትምህርት የጀመሩ ተማሪዎች አቋራጮችን አግባብተው እንዲያመጧቸው እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል። መምህራንም ዘግይተው ትምህርት የጀመሩትን ተማሪዎች ለማብቃት በትርፍ ጊዜያቸው ጭምር እያስተማሩ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን በ2017 የትምህርት ዘመን 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ቢታቀድም ክልሉ የገጠመው የጸጥታ ችግር ዕቅዱ እንዳይሳካ እንቅፋት መኾኑን ለአሚኮ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥትም ለትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት ለሁለተኛ ጊዜ ባደረገው የምዝገባ ንቅናቄ ከ2 መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ማስተማር መቻሉን ኃላፊው አስታውሰዋል።

መማር የሚችሉ ግን ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው የቆዩ ተማሪዎችን የዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ለሦስተኛ ጊዜ በተደረገው የንቅናቄ ዘመቻ ሰሜን ወሎ ዞን 19 ሺህ 248 እና ሰሜን ጎጃም ዞንም 12 ሺህ 268 ተማሪዎችን መዝገበው ማስተማራቸውን በአርዓያነት ኀላፊው አንስተዋል።

እንደ ክልልም በሦሥተኛው ዙር የተማሪዎች ምዝገባ ዘመቻ ራዕያቸው የጨለመባቸውን 72 ሺህ 379 ተማሪዎች በመመዝገብ የመማር ተስፋቸው ዳግም እንዲገለጥ ተጨማሪ ዕድል እንደተፈጠረላቸዋል አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።

የእነ ተማሪ የክቴ አያሌው የጨለመ ተስፋም የተገለጠው በሦስተኛው ዙር ምዝገባ መኾኑን ልብ ይሏል።

ያልተመዘገቡ ተማሪዎች ከትምህርት ማዕድ ተቋዳሽ እንዲኾኑ ለማድረግም ቀጣይ የንቅናቄ ሥራ እንደሚኖር ነው አቶ ጌታቸው የተናገሩት።

መማር ማስተማር በትምህርት ተቋማት ብቻ የሚከናወን አይደለም ያሉት ኃላፊው ኀብረተሰቡ ትምህርት ቤቶችን በባለቤትነት ይዞ መደገፍ ይገባዋል። ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ በመኾኑ ሲቋረጥ ሁሉም አካል ሊቃወም ይገባዋል ነው ያሉት።

የዓለም ሀገራት የበለጸጉት በተዓምር አለመኾኑን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው ዛሬ ትምህርት እንዲቋረጥ ማድረግ ማለት ነገ ለትውልዱ ድህነትን ማውረስ ነው።

አቶ ጌታቸው አክለውም አሁንም በክልሉ 59 በመቶ የሚኾኑ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ይገኛሉና ማንኛውም ወገን እነዚህን ተማሪዎች የማስተማር የሞራልም የሕግም ግዴታ አለበት ነው ያሉት።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአፋር ክልል የግብርና እና የኢንዱስትሪ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ።
Next articleየኢትዮጵያ ምልክት የኾኑትን ዋሊያዎች ከአደጋ የመጠበቁ ሥራ