የካቲት 12 ሜዲካል ኮሌጅ በተለያዩ የሕክምና ዘርፎች ያሠለጠናቸውን 186 ተማሪዎች አስመረቀ።

30

አዲስ አበባ: መጋቢት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኮሌጁ በመደበኛና በማታ መርሐ ግብር ለ8ኛ ዙር ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ነው በዛሬው እለት ያስመረቀው።

የኮሌጁ ተወካይ ዶክተር አንተነህ ምትኩ ኮሌጁ በሕክምና እና በጤና ሳይንስ ዘርፍ በውስጥ ደዌ፣ በቀዶ ጥገና፣ በአፍ ውስጥ ሕክምና እና የኅብረተሰብ ጤናን ጨምሮ በተለያዩ 19 የትምህርት መስኮች የጤናውን ሥርዓት የሚያሳልጡ ብቁ ባለሙያዎችን ለመፍጠር እየሠራ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ያለውን እንቅስቃሴ ለማገዝ የየካቲት 12 ሜዲካል ኮሌጅ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኀይል በማፍራት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማ አሥተዳደሩ በሽታን የመከላከል እና አክሞ የማዳን ፓሊሲን እየተገበረ ነው ብለዋል። በተለይም በሽታን ከመከላከል አኳያ ከተማዋን ከብክለት በመታደግ ጽዱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑንም ገልጸዋል።

ከተማዋን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም በዘርፉ የተማረ የሰው ኀይልን ወደ ሥራ ማስገባት ወሳኝ ነው ብለዋል። ከንቲባዋ አክለውም ተመራቂዎች ሙያውን አክብረው በቅንነት ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በተገኙበት የሜካናይዝድ ሙያተኞችን እያስመረቀ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአፋር ክልል የግብርና እና የኢንዱስትሪ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ።