
ሰቆጣ: መጋቢት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016/17 የክረምት ወቅት በተፈጠረው የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በጋዝጊብላ፣ ድሃና እና ጻግቭጂ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለችግር ተዳርገዋል። የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ በርናባስ በካናዳ ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያን በተገኘ ድጋፍ 370 ኩንታል እህል ለጋዚጊብላ ወረዳ ነዋሪዎች አስረክበዋል። የተደረገው ድጋፍ 5 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ወጭ እንደተደረገበት ተመላክቷል።
ከአሁን በፊትም በጻግቭጂ ወረዳ እና በድሃና ወረዳ ተመሣሣይ ድጋፍ አድርገዋል። በአጠቃላይ ከ1 ሺህ 200 ኩንታል በላይ የእህል እና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል። የተደረገው ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ የተናገሩት ብጹዕ አቡነ በርናባስ ድጋፉን ላበረከቱት በካናዳ ለሚኖሩ ወገኖች ምስጋና አቅርበዋል።
የጋዝጊብላ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አበባው ደሳለኝ በወረዳው በርካታ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።
ብጹዕ አቡነ በርናባስ ያደረጉት 370 ኩንታል እህልም ከ2 ሺህ 400 በላይ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የወር ቀለብ እንደሚኾን ገልጸዋል። ድጋፉ የተደረገላቸው የ09 ቀበሌ ነዋሪው ጸጋው ፈረደ ባለፈው ክረምት በነበረው የጎርፍ አደጋ መኖሪያ ቤታቸውን ጨምሮ ማሳቸው ከጥቅም ውጭ እንደኾነባቸው ተናግረዋል። የተደረገው ድጋፍ ለጊዜውም ቢኾን የቤተሰቦቼን ሕይዎት ታድጎልኛል ነው ያሉት። መንግሥት እና አጋዥ ድርጅቶች ሊደርሱላቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል።
ሌላኛዋ የአበርገሌ ወረዳ 01 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ ተማረ ብጹዕ አቡነ በርናባስ ስላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። የሚደረጉ ድጋፎች እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስተና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ ዝናሽ ወርቁ በደጋማ አካባቢዎች በደረሰው የተፈጥሮ አዳጋ ምክንያት በርካታ ወገኖች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት።
በመጀመሪያ ዙር ከ119 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንደተደረገም ጠቁመዋል። በብጹዕ አቡነ በርናባስ አማካኝነት በሦስቱ ወረዳዎች ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ከ1 ሺህ 200 ኩንታል በላይ የእህል ድጋፍም ተደርጓል ብለዋል። ከ8 ሺህ በላይ የሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችም የድጋፉ ተጠቃሚ ኾነዋል ነው ያሉት።
ድጋፉን ላደረጉት ለ ብጹዕ አቡነ በርናባስም ምስጋና አቅርበዋል። ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች አጋዥ ድርጅቶችና መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!