145 የስጋ ከብቶችን የሚያደልበው ስኬታማ ወጣት ተሞክሮ።

32

ጎንደር: መጋቢት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች በእንስሳት ማድለብ ሥራ ላይ በመሠማራት ተጠቃሚ እየኾኑ መጥተዋል። ወጣት ወንድም ባይነሳኝ በከተማዋ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ 15 ከብቶችን በማድለብ ነበር ሥራውን የጀመረው።

ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ቦታ ተከራይቶ በርካታ እንስሳትን በማድለብ እና ካፒታሉን በማሳደግ መኖሪያ ቤቱን በመገንባት ከዘርፉ ተጠቃሚ መኾን እንደቻለ ገልጾልናል። ከታላላቅ ወንድሞቹ ልምድን በመቅሰም ጠንካራ የሥራ መንፈስን በመላበስ ውጤታማ መኾን እንደቻለ ያነሳው ወጣት ወንድሙ ለ2017 ዓ.ም የፋሲካ በዓል 145 ከብቶችን በማድለብ ለገበያ ለማቅረብ እየሠራ መኾኑን አስረድቷል። ከራሱ አልፎ ለ30 ግለሰቦች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አንስቷል።

በቀጣይ የእንስሳት ምርትን ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳለው ያነሳው ወጣቱ መንግሥት የሥራ ቦታ እንዲሰጠው እና የውጭ ገበያ ትስስር እንዲፈጥርለትም ጠይቋል። ወጣቶች በዘርፉ ቢሠማሩ ተጠቃሚ መኾን እንደሚችሉ የጠቆመው ወጣት ወንድሙ ወጣቶች ጊዜ እና ጉልበታቸውን በመጠቀም ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችሉም ተናግሯል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ እና የእንስሳት ምርት ተዋጽኦ ባለሙያ መላኩ ደምሌ በከተማ አሥተዳደሩ ከ6 ሺህ በላይ ወጣቶች በእንስሳት ማድለብ ሥራ ላይ መሠማራታቸውን ገልጸዋል። የተሻሻሉ የመኖ ምርቶችን በማቅረብ፣ ለእንስሳቱ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት፣ የተሻለ ዝርያ ያላቸውን ለአድላቢዎች በማቅረብ እና በክላስተር እንዲሠሩ በማድረግ ዘርፉን ለማዘመን እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በከተማዋ ከብት በማድለብ የሚገኘው የስጋ ምርት እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል። በከተማዋ 145 እንስሳትን በማድለብ ለሌሎች አርአያ መኾን የቻለውን ወጣት የቦታ ችግር ለመቅረፍ ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል። የውጭ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከአጋር አካላት ጋር በቅርበት እየተሠራ ነውም ብለዋል።

ዘጋቢ: ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕዝብን በቅንነት ለማገልገል እንደሚሠሩ የወልድያ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች ተናገሩ።
Next articleብጹዕ አቡነ በርናባስ በጋዝጊብላ ወረዳ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ አደረጉ።