“የሕዳሴ ግድቡ ሁሉንም ለአንድ ዓላማ ያሰለፈ ሀገር የምትኮራበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው” አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር)

20

ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን እስካሁን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 21 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ እየተገነባ ያለ ትልቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክት ነው።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከግብ እንዲደርስ ዜጎች በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው እና በጉልበታቸው አጋርነታቸውን በቁርጠኝነት እያሳዩ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የግድቡ ግንባታ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) “የሕዳሴ ግድቡ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ለአንድ ዓላማ ያሰለፈ ሀገር የምትኮራበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው” ብለዋል። በተለይም ኅብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ ድጋፎች ከድህነት ለመላቀቅ እና ለማደግ ያለውን ፍላጎት በተግባር ያሳየበት መኾኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ከ21 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ኢዜአ እንደዘገበው ሕዝቡ በሀብት ከሚያደርገው እገዛ ባለፈ 120 ቢሊዮን ብር የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እድገቷን የሚያረጋግጡ ያልተነኩ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች አሏት ያሉት ዳይሬክተሩ ፀጋዎቿን ጥቅም ላይ ለማዋል የልማት ሥራዎችን ቀርጸን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል። በቀጣይም የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ከጫፍ እንዲደርስ ዜጎች ለፕሮጀክቱ እያደረጉት ያለውን የተለያዩ ድጋፎች አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“አሚኮ ስሁት ትርክቶችን ለማረም እና ኅብረብሔራዊት ኢትየጵያን ለመገንባት እየሠራ ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next articleየአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እንዲኾን በትኩረት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።