ለብሔራዊ ፈተና ተገቢውን ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ተፈታኝ ተማሪዎች ተናገሩ።

24

ደብረታቦር: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን በደብረ ታቦር ከተማ የዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተፈታኝ ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡

አሚኮ የተማሪዎችን የሀገር አቀፍ ፈተና ዝግጅት በተመለከተ በትምህርት ቤቱ በመገኘት ምልከታ አድርጓል። ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት በተጨማሪ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ መኾኑንም ተማሪዎቹ ነግረውናል።

በመምህራን እየተዘጋጁ የሚሰጣቸውን የመለማመጃ ጥያቄዎችን በጋራ በመሥራት ለተሻለ ውጤት እየተዘጋጁ መኾኑን ገልጸዋል። ከትምህርት በተጨማሪ የሥነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ የምክር አገልግሎት ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

የማጠናከሪያ ትምህርቱን እየሰጡ ያገኘናቸው የእንግሊዝኛ መምህርት ሙሉ ደሳለኝ የተመረጡ ጥያቄዎችን በማዘጋጀት ተማሪዎች በጋራ እንዲሠሩ በማድረግ ለሀገር አቀፍ ፈተናው እያዘጋጇቸው መኾኑን ነው የተናገሩት።

ሌላው ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጡ ያገኘናቸው በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የእግሊዝኛ ቋንቋ እና ሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ኀላፊ መምህር ጌታቸው ደጌ ተማሪዎች ለብሔራዊ ፈተና እንዲዘጋጁ እያገዙ መኾኑን ተናግረዋል።

የዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቤተ መጻሕፍህ አስነባቢ ፈንታዬ ቢሰጥ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ከሰኞ እስከ እሑድ ቤተ መጻሕፍቱ ሙሉ ጊዜውን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የተማሪዎች የጊዜ አጠቃቀምም መልካም እንደኾነ ነው የገለጹት።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እየበሩ አዕምሮ የማጠናከሪያ ትምህርቱ ተማሪዎችን ለውጤት የሚያዘጋጅ ነው ብለዋል።

እየተሰጠ ካለው የማጠናከሪያ ትምህርት በተጨማሪ የአዳር ጥናት ለማስጀመር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ የነፃ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው።
Next article“አሚኮ ስሁት ትርክቶችን ለማረም እና ኅብረብሔራዊት ኢትየጵያን ለመገንባት እየሠራ ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ