የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የነፃ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው።

10

ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል “ኪውር ብላይንድነስ” ከተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ነፃ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት በአይራ ጠቅላላ ሆስፒታል እየሰጠ ነው።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ.ር) የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 100ኛ ዓመት እና የዩኒቨርሲቲውን 70ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የኅብረተሰቡን ችግር በመለየት ነፃ የዐይን ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ገልጸዋል።

የዐይን ሞራ ቀዶ ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ዩኒቨርሲቲው ኪውር ብላይንድነስ ከተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም አስረድተዋል። በዚህም ለበርካታ ዓመታት የዐይን ብርሃናቸውን አጥተው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ማግኘት በመቻላቸው የዐይን ብርሃናቸው እንዲመለስ አስችሏል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዚህም ብቻ ሳይኾን በሌሎችም ነፃ የማኅበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የጤና መምሪያ ኀላፊ ገበያው አሻግሬ በአይራ ጠቅላላ ሆስፒታል እየተሰጠ ባለው ነፃ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና የዓይን ነጻ ግርዶሽ ተጠቂ የኾኑ ወገኖች አገልግሎት እያገኙ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ሕክምናውን እያገኙ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከስምንት ወረዳዎች ተለይተው የመጡ ናቸው። እስካሁን ከ300 በላይ የሚኾኑት የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተሠርቶላቸዋል ብለዋል። የትራኮማ እና የዐይን ሞራ ግርዶሽ በሽታዎችን ለመከላከል ከጤና ኤክስቴንሽን ጀምሮ የተቀናጀ የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

በአይራ ሆስፒታል እየተሰጠ በሚገኘው የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት 97 የሚደርሱ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ታካሚዎች አገልግሎቱን እንዳገኙ የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ከተማ ጤና መምሪያ ኀላፊ ሰኢድ የሻው ናቸው።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዐይን ሕክምና ፕሮጀክቶች አስተባባሪ ሰማልኝ አባው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ “ኪውር ብላይንድነስ” ከተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር እየተሰጠ ባለው ነፃ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና 946 ሕሙማን የዐይን ብርሃናቸው እንዲመለስ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። እስካሁን 400 የሚኾኑ ወገኖች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና ተደርጎላቸው ነው ያሉት።

የዐይን ሞራ ሕክምና የሚደረግላቸው ሕሙማን ከሕክምናው በተጨማሪ በሆስፒታሉ በሚቆዩበት ጊዜ የምግብ እና የትራንስፖርት ወጭ እንደተሸፈነላቸውም ገልጸዋል። በዩኒቨርስቲው የዐይን ሕክምና ስፔሻሊስት፣ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ እና የዐይን ሞራ ግርዶሽ ልዩ ሳብ ስፔሻሊስት ዶክተር ወሰን ሙሉጌታ ማየት የተሳናቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በተደረገላቸው ሕክምና በሞራ ተሸፍኖ የነበረው የዐይን ብሌናቸው እንዲስተካከል መደረጉን ገልጸዋል። በሙያቸው ደስ ብሏቸው እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

ነፃ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና ተጠቃሚ የኾኑት መላከፀሐይ እንግዳ ብርሃናቸው በመመለሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል። የዐይን ብርሃናቸውን ለሁለት ዓመት አጥተው እንደቆዩ አንስተዋል። አሁን ግን በአይራ ሆስፒታል በተደረገላቸው ነፃ የዐይን ቀዶ ሕክምና አገልግሎት የዐይን ብርሃናቸው በመመለሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ ድምቡሉ ጎሼ ለሁለት ዓመት ዐይናቸው ብርሃን በማጣቱ ምክንያት የግብርና ሥራቸውን ለማከናወን፣ ወጥተው ለመግባት ተስኗቸው ለጥገኝነት ተዳርገው መቆየታቸውን አስታውሰዋል። አሁን በተደረገላቸው ሕክምና የዐይናቸው ብርሃን ተመልሶ ማየት በመጀመራቸው ምሥጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ደስታ ካሳ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበ2017 ዓ.ም ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዷል።
Next articleለብሔራዊ ፈተና ተገቢውን ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ተፈታኝ ተማሪዎች ተናገሩ።