በ2017 ዓ.ም ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዷል።

23

አዲስ አበባ: መጋቢት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የደን ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በውይይት እየተከበረ ነው። የዓለም የደን ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ማኅበረሰቡን ለደን ልማት ጥበቃ፣ አጠቃቀም እና የዘርፉን ብዝኀ ጥቅም በሚያሳይ መልኩ እና ግንዛቤን ለማሳደግ በሀገራት ተከብሮ ይውላል።

የዘንድሮው 14ኛው ዓለም አቀፍ የደን ቀንም “ደን እና ምግብ” በሚል መሪ መልዕክት በኢትዮጵያ በመከበር ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ የደን ልማት ቀኑን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የዓለም አቀፍ እና የሀገር አቀፍ ደረጃ የደን ልማት እጥረት ያስከተለውን ተግዳሮት በተመለከተ ውይይት እየተደረገ ነው።

ኢትዮጵያ ከ26 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የደን ሀብት እንዳላት የገለጹት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ ምንቴ (ዶ.ር) የደን ሀብቱ ለአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች አስተዋጽኦው ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ ከ40 ቢሊዮን በላይ የተለያዮ ዝርያ ያላቸው የጥምር ደን ችግኞች መተከላቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሰው በ2017 ዓ.ም ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋቸታቸውን ገልጸዋል።

የደን ልማት በዓለም ላይ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ለሚኾኑ ሕዝቦች የኑሮ መሠረት ኾኗል ያሉት የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም ናቸው። በዓለም ኢኮኖሚ ላይም የደን ሀብት አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ያለው የደን ሀብት ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚኾነው ለአርሶ አደሮች አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የደን ሀብትን ለማሳደግ ቀኑን ከማክበር ባለፈ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤን በመፍጠር በደን ሽፋን የመሬት መሸርሸርን የውኃ እና የአየር መበከልን ለመከላከል አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በማጠናከር በትኩረት ይሠራል ሲሉም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ራሔል ደምሰው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleትኩረት ያጣው የዐዕምሮ ጤና!
Next articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ የነፃ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው።