
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጣርማበር ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ፋንታዬ ገሰሰ ለ2017/18 የምርት ዘመን መሬታቸውን ለሰብል ምርት እያዘጋጁ ስለመኾናቸው ተናግረዋል፡፡ ለምርት ጭማሪ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማዘጋጀት እና የተለያየ አሠራርንም ለመተግበር መዘጋጀታቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ካለመቅረቡም በላይ በአቅራቢያቸዉ የአቅርቦት ማዕከላት ባለመኖራቸዉ እየተቸገሩ መኾናቸዉን ነዉ ያስረዱት፡፡ ሌላዉ አሚኮ ያናገራቸዉ የአንኮበር ወረዳ ነዋሪዉ ገረመዉ አስረስ አካባቢያቸዉ በልግ አምራች እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ ይህ እንዳለ ኾኖ ለመኸር እርሻ እየተዘጋጁ መኾናቸዉን ተናግረዋል፡፡
ለዚህ የሚያግዛቸዉን የአፈር ማዳበሪ ለማሟላት እየሞከሩ ቢኾኑም በሚፈለገዉ ልክ አቅርቦት እንደሌለ ነዉ የተናገሩት፡፡ “በ2017/18 የመኸር የምርት ዘመን ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታዉቋል፡፡
ዞኑ በ2017/18 የመኸር የምርት ዘመን 549 ሺህ ሄክታር መሬትን በዘር በመሸፈን 17 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ስለመታቀዱ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ ተናግረዋል። የታቀደውን ምርት ለማምረት እና ለምርታማነት አጋዥ የኾኑ ግብዓቶች አቅርቦት ሥራዎችም ቀደም ብለው ስለመጀመራቸው ነዉ ያስረዱት፡፡
የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ አሲዳማ አፈርን ማከም እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትን ጨምሮ የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ ነው ብለዋል። ለምርት ዘመኑ ለዞኑ 1 ሚሊዮን 129 ሺህ 800 ኩንታል የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ስለመፈፀሙም አቶ ታደሰ ገልጸዋል።
ከተገዛው ውስጥ 331 ሺህ ኩንታል ወደ ዞኑ ስለመግባቱ እና ወደ ወረዳዎች የማድረስ እና ለአርሶ አደሮች የማሰራጨት ሥራዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል።
አርሶ አደሮች ላነሱት በቂ አቅርቦት አለመኖር ጉዳይ በተመለከተ ከስር ከስር የሚገባዉን ማዳበሪያ እያሰራጨን እንገኛለን ነዉ ያሉት፡፡ ሙሉ በሙሉ እስከ ግንቦት መጀመሪያ የማዳበሪያ ስርጭቱ ለማጠናቀቅ እንደሚሠራም ኀላፊው ተናግረዋል። ከ2016/17 የምርት ዘመን የተረፈ ተጨማሪ 174 ሺህ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ መኖሩን ያነሱት ኀላፊው ካለፉት ዓመታት አንፃር ዘንድሮ የተሻለ አቅርቦት አለን ብለዋል።
ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል አቶ ታደሰ። በዚህም ለምርት ዘመኑ 9 ሚሊዮን ሜትርኪዩብ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትርኪዩብ ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል።
የሰው ሠራሽ ማዳበሪያውም ቀድሞ እንዲደርስ እና ከሕገ ወጥ ንክኪ አካሄድ ነፃ በኾነ አግባብ እና በፍትሐዊነት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እንዲኾን መምሪያው ኀላፊው በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን