“ደሴ ከተማ ተጨባጭ የኾኑ ለውጦችን እያስመዘገበች ነው” አሕመዲን መሐመድ ( ዶ.ር)

30

ደሴ: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ የአማራ ክልል የከተማ ዘርፍ ተቋማት መሪዎች የመስክ ጉብኝት አድርገዋል። በደሴ ከተማ የመስክ ጉብኝት ያደረጉት የአማራ ክልል የከተማ ዘርፍ ተቋማት መሪዎች በከተማዋ እየተካሄዱ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለሌሎች መሰል ግንባታዎች ምሳሌ መኾን የሚችል መኾኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከወሎ ባሕል አምባ እስከ ሮቢት ድረስ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት የደሴ ከተማን የነገ ተስፋ ያመላከተ መኾኑን አንስተዋል። ደሴ ከተማ በስማርት ሲቲ የተጓዘችበት ርቀት የሚያስመሰግን ነው ያሉት መሪዎቱ በተለይም የከተማና የመሰረት ልማት አገልግሎትን ለማዘመን የተሠሩ ሥራዎች የሚበረታቱ ስለመኾኑን አንስተዋል።

በኢንቨስትመንት በኩልም በአዲስ መልክ ሥራ የጀመሩ ፋብሪካዎች የኅብረተሰቡን ችግር ፈች መኾናቸውን ተናግረዋል። ደሴ ከተማን እንደ አዲስ መሥራት አስቸጋሪ ቢኾንም መሪው በተቀናጀ መልኩ በመሥራቱ ይህንን ማሳካት ችሏል ያሉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኅላፊ አሕመዲን መሐመድ ( ዶ.ር) ይህም ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግቧል ብለዋል።

በስማርት ሲቲ ግንባታው ደሴ ከተማ አገልግሎትን በማዘመን በኩል የሚያበረታታ ተግባር ፈፅሟል ያሉት ዶ.ር አሕመዲን ተግባሩ ወደ ክፍለ ከተማና ቀበሌ መውረድ አለበት ሲሉ ተናግረዋል። የደሴ ኮሪደር ልማት ለደሴ ከተማ እድገት ለብዙ ዓመታት መሰረት የሚጥል የተቀናጀ የልማት ሥራ ነው ያሉ ሲኾን ደሴ ከተማ ተጨባጭ የኾኑ ለውጦችን እያስመዘገበች ነው ብለዋል።

በተለይም ኅብረተሰቡን የልማቱ አካል በማድረግ የተሠራው ሥራ ለሌሎች አካባቢዎችም በተሞክሮ የሚወሰድ መኾኑን አብራርተዋል።

ዘጋቢ:- አበሻ አንለይ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበምርት ዘመኑ 17 ሚሊዮን ኩንታል የምርት ጭማሪ እንዲኖር አቅዶ እየሠራ መኾኑን ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
Next articleማዳበሪያን በፍትሐዊነት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው።