
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2017/18 ምርት ዘመን የመኽር ሰብል ፓኬጅ የአሠልጣኞች ሥልጠና እና የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየሰጠ ነው።
በሥልጠናው ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ሥልጠናው በምርምር የተገኘውን የአፈር ለምነት ማሻሻያ ለውጦች በማስተዋዎቅ ሰልጣኞች አዳዲስ ዕውቀትን ገብይተው እና ብቃት ፈጥረው በመውጣት ለምርት ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያለመ ነው ብለዋል።
ሠልጣኞች ክልሉን ከገባበት ችግር ውስጥ ፈጥኖ ለማውጣት የግብርናው ዘርፍ ውጤታማ መኾን አለበትም ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው። ክልሉ ምን ጊዜም በኢኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገበ የሰላም እጦት ችግር አይገጥመውም ነው ያሉት። የግብርናው ዘርፍ ዘምኖ፣ አርሶ አደሩ ተመግቦ ማደር ሲችል እና የመግዛት አቅም ሲጨምር የምግብ ዋስትና የሚረጋገጥበት ደረጃ ሲደረስ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚቻል ዶክተር ድረስ ተናግረዋል።
በእርሻው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ባላሳካናቸው ጉዳዮች ቁጭት ውስጥ በመግባት በአጭር ጊዜ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት ቀን እና ሌሊት መሥራት ይገባል ብለዋል። እንደ ሀገር የአማራ ክልል በሰብል ምርት ረገድ 33 በመቶ የማቅረብ ድርሻ አለው ያሉት ዶክተር ድረስ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ አፈር የተሻለ ምርት እንዲሰጥ በግብዓት እና ቴክኖሎጅ ታግዞ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ባለፈው የምርት ዘመን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚኾኑ አርሶ አደሮች ሙሉ የግብርና ፓኬጆች ተጠቃሚ ኾነዋል። ያም በመኾኑ ከዕቅዱ ወደ 25 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ምርት ተገኝቷል ብለዋል። ባለፈው የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት በክልሉ ታይቶ በማይታወቅ ኹኔታ 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ማዳበሪያ በማሰራጨት በሄክታር 28 ኩንታል የነበረውን ምርት በሄክታር ወደ 32 ኩንታል ማሳደግ እንደተቻለ ዶክተር ድረስ ተናግረዋል።
ስልጠና ብቻውን ጥቅም የለውም ያሉት ዶክተር ድረስ ሠልጣኞች እንደ ሀገር በቁጭት ክልሉ የገጠመውን ችግር ታሳቢ ያደረገ ተረጅነትን የማስወገድ፣ ምርታማነትን የማስፈን እና በጸረ ድህነት ትግል የግብርና ምርታማነት ዘመቻ መፈጠር አለበት ነው ያሉት። በግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ቀኛዝማች መስፍን እየተሰጠ ያለው ሥልጠና በ2017/18 የሰብል ምርትን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
“በምርት ዘመኑ 17 ሚሊዮን ኩንታል የምርት ጭማሪ እንዲኖር ታቅዶ እየተሠራ ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በአግባቡ መጠቀም፣ የተሻሻሉ ፓኬጆችን መተግበር፣ ለፈጻሚው አካል የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እስከ አርሶ አደሮች ድረስ መስጠት ተገቢ ኾኖ ተገኝቷል ብለዋል።
“ከዚህ በፊት እንጠቀመው የነበረውን የኤን ፒ ኤስ የአፈር ማዳበሪያ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በዳፕ እንዲቀየር በምርምር ተወስኗል። በጉዳዩ ዙሪያም በጥናት የተደገፈ ሳይንሳዊ ሥልጠና እየተሰጠ ነው” ብለዋል ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመጡት ሠልጣኝ ባለሙያ ዓለማየሁ ሙሉጌታ የሰብል ልማት ፓኬጆችን በየጊዜው በሥልጠና በመተግበራችን በየዓመቱ የምርት ጭማሪ ማስመዝገብ ችለናል ነው ያሉት።
አሁን እየተሰጠ ያለውን ሥልጠናም ታች ድረስ በማውረድ በምርት እና ምርታማነት ዙሪያ አዎንታዊ ውጤት እንዲመዘገብ የሚኖረው ፋይዳ ላቅ ያለ ይኾናል ብለዋል። ከግብዓት አጠቃቀም ጀምሮ ያለውን የቴክኖሎጂ ድጋፍ ባለሙያውም ኾነ አርሶ አደሩ በስልጠና ታግዞ ከተጠቀመ ከዕቅድ በላይ ምርት ይመዘገባል” ነው ያሉት።
ዘጋቢ: ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!