ነጻ የሕግ አገልግሎቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ የማኅበረሰብ ክፈሎችን ተጠቃሚ ያደረገ መኾኑ ተገለጸ።

12

ደባርቅ: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አቅም ያገናዘበ እና የፍትሕ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መኾኑንም የደባርቅ ወረዳ ፍርድ ቤት ገልጿል። ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብ እና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት እንዳለው የሀገሪቷ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37 ይደነግጋል።

የደባርቅ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መገናኛ ሞላ ተገልጋዮች ሕጋዊ አካሄዱን ጠብቀው በተገቢው መንገድ የፍርድ ውሳኔ እንዲያገኙ ከሕግ ዕውቀት አንጻር የተገናዘቡ ጉዳዮችን ለፍትሕ ተቋማት ለማቅረብ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱ አስተዋጽኦው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል። ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ነጻ አገልግሎት በመስጠት በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ሊደርሱ የሚችሉ መጉላላቶችን ለማስቀረት ያስችላል ነው ያሉት።

የአገልግሎት አሥተባባሪው መምህር ሸጋው ብርሃኑ የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያላቸውን ውስን ጊዜ በማጣበብ በሕግ ድጋፍ አገልግሎቱ እየተሳተፉ እንደሚገኙም ገልጸዋል። አገልግሎቱ ተማሪዎቹ በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር እንዲያዳብሩ ዕድል የሚሰጥ እንደኾነም አብራርተዋል።

ተማሪዎቹ በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መሳተፋቸው ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲተዋወቁ እና ማኅበራዊ ግንዛቤያቸውን እንዲያጎለብቱ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል። ተሳታፊ ተማሪዎቹም ተገልጋዩን ማኅበረሰብ በተማሩት የሕግ ትምህርት በማገዛቸው ደስተኛ መኾናቸውን አንስተዋል። ለቀጣይ የሥራ ዘመናቸው ግብዓት የሚኾኑ በርካታ የሕይዎት ተሞክሮዎችን መቅሰም እንዳስቻላቸውም አብራርተዋል።

የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ተጠቃሚዎችም እየተደረገላቸው ባለው ተግባር ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። የደባርቅ ከተማ ነዋሪው አቶ እሸቴ ሙሉ በቀጣይም አገልግሎቱ የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። ሌላኛዋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ ማዕዛ ምስጋናው እየተደረገ ያለው የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ለአሁን ብቻ ሳይኾን ወደፊትም ልምድ እና ዕውቀት እንድናዳብር የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት የሰሜን ጎንደር ዞን ፍርድ ቤት እና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አብሮ ለመሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተከዜ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ትሩፋቶችና መሰናክሎቹ
Next articleበምርት ዘመኑ 17 ሚሊዮን ኩንታል የምርት ጭማሪ እንዲኖር አቅዶ እየሠራ መኾኑን ግብርና ቢሮ አስታወቀ።