የተከዜ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ትሩፋቶችና መሰናክሎቹ

11

ሰቆጣ: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተከዜ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ከ9 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሜትር ኪብ ውኃ የመያዝ አቅም አለው። ከ17 ዓይነት በላይ የዓሳ ዝርያዎች በውስጡ ይዟል። በዓመት ከ10 ሺህ ቶን በላይ የዓሳ ምርት ይመረትበታል።

ነገር ግን በአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር ያለውን ፀጋ አሟጦ መጠቀም እና የተደራጁ ወጣቶችን በሥርዓት እንዲጠቀሙ ማድረግ አልተቻለም። የዓሳ ማስገር ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ግን በችግር ውስጥም ቢኾኑ አሁንም መሥራታቸውን ቀጥለዋል።

ወጣት ክፍሌ መኳንንት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ዓሳ በማስገር የሚተዳደር ሲኾን የተሻለ ገቢ እንደሚገኝ ገልጿል። 1 ኪሎ ዓሳ ከ150 እስከ 180 ብር እንደሚያስረክቡ የገለጸው ወጣቱ አብዛኛዎቹ ባለሃብቶች ከትግራይ ክልል የሚመጡ በመኾናቸው ወጣቱ በፈለገው ገበያ ማስረከብ አልቻለም ብሏል።

ሌላኛው አስጋሪ ወጣት ወልዴ ተክሌ ዓሳ በማስገር ከ10 ዓመት በላይ እንደኾነው ነግሮናል። በዚህም ቤተሰቦቹን ከመርዳት ባሻገር ለትራንስፖርት የሚያገለግል ጀልባ እና የዓሳ ማስገሪያ ገንዳ በግሉ እንደገዛ ገልጿል። በቀጣይም ተረካቢ የመኾን ሕልም እንዳለው የገለጸው ወጣቱ ከአብርገሌ ሲቀላ – ተከዜ የሚወስደው መንገድ የተበላሸ መኾኑ ዓሳው ለተፈለገው ገበያ ሳይደርስ እየተበላሸብን ነው ብሏል።

በአብርገሌ ወረዳ ከ1 ሺህ 900 በላይ ወጣቶች በአንድ ማኅበር ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡ ቢኾንም የተከዜ ሐይቅ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ባለመኾኑ የተነሣ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማሰማራት መቸገሩን የወረዳው እንሰሳትና ዓሳ ሃብት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቀኘይ እነተ ገልጸዋል።

መሠረተ ልማቱን ለመጠገን ቅድሚያ አካባቢውን ሰላም ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲሳይ አያሌው ናቸው። በአካባቢው የተጀመረው የሰላም ስምምነት በማጽናት የተከዜን ዓሳ ለተደራጁ ወጣቶች እና አካባቢ በቀል ባለሃብቶችን ለማሠማራት ተዘጋጅተናል ያሉት ኀላፊው ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር የተበላሹ መንገዶችን ለመጠገን በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን ለማቅረብ እየሠራ መኾኑን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleነጻ የሕግ አገልግሎቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ የማኅበረሰብ ክፈሎችን ተጠቃሚ ያደረገ መኾኑ ተገለጸ።