
ደብረታቦር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ እንዳስታወቀው የአርሶ አደሮችን ፍላጎት እና የአካባቢውን የአየር ንብረት መሠረት በማድረግ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ ነው።
የተለያየ ዝርያ ያላቸውን ተክሎች በማዳቀል ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግም ትኩረት የተደረገበት ተግባር እንደኾነም ነው መምሪያው ያስታወቀው።
በችግኝ ጣቢያው ተገኝተን ያነጋገርናቸው ሠራተኞች ለአካባቢው አየር ንብረት ተስማሚ እና የነዋሪዎችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የተለያዩ የአትክልት እና ፍራፍሬ ዝርያዎችን እያፈሉ መኾኑን ተናግረዋል። የተፈጠረላቸው የሥራ ዕድልም ኑሯቸውን ለመምራት እንዳገዛቸው ነው የገለጹት።
ከዚህ በፊት የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኝ ጣቢያ እንዳልነበር ያስታወሱት በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያ ካሳሁን ክንዳለም በአጭር ጊዜ የሚደርሱና በሽታ መቋቋም የሚችሉ መሠተ ግንዶችን ከፍሬ-ሰጦች ጋር የማዳቀል ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።
በተመጣጣኝ ዋጋም ለኅብረተሰቡ እያቀረቡ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች ችግኞችን በማስመጣት በችግኝ ጣቢያው እንደ አፕል፣ አቮካዶ፣ ቡና እና ሌሎችንም ችግኞች ለማልማት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ደግሞ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው ይበልጣል ናቸው።
መምሪያ ኀላፊው ከችግኝ ልማት ጎን ለጎን አትክልት እና ፍራፍሬዎችን በማልማት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!