
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የፖለቲካ እና የድርጅት ሥራዎችን ዕቅድ አፈጻጸም በባሕር ዳር ከተማ እየገመገመ ነው።
በግምገማ እና ውይይት መድረኩ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና ሌሎችም የፓርቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
መርሐ ግብሩ በሚኖረው ቆይታ ባለፉት ስምንት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች ቀርበው ጥንንካሬ እና ውስንነቶቻቸውን በመለየት የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይም ይመከራል። በመድረኩ መጀመሪያ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን ወቅታዊ የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ጨምሮ ባለፉት ስምንት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች ቀርበው ይገመገማሉ ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ላይ የተቀመጡ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎችም በጥልቀት ተገምግመው የቀጣይ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ነው ያሉት። በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የትምህርት ሥራውን በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቷል፤ በዛሬው መድረክ ላይ የትምህርት ሥራችንን ተግዳሮቶች ለመለየት እና ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ የሚያስችል ውይይት ይደረጋል ብለዋል።
ሕዝቡ ማዳበሪያ እና መሰል መሠረታዊ አቅርቦቶች ሲዘገዩ ጠንክሮ ይጠይቃል፣ ይሞግታልም፤ የልጆች ትምህርት ሲቋረጥ ግን በጉዳዩ አሳሳቢነት ያህል ሲጠይቅ እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ሲታገል አይታይም ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። ከዕውቀት መለያየት የድህነት መጀመሪያ መኾኑን እና ትምህርት ደግሞ የሁሉም ነገር መሠረት መኾኑን በውል መረዳት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ስለተቋረጠው የልጆች ትምህርት በትኩረት መመካከር እንዳለበት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአጽንኦት ተናግረዋል። በዛሬው መድረክ ላይ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚበጅ ጠንካራ ፓርቲ ለመመሥረት በሚያስችሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይም ውይይት ይደረጋል ብለዋል።
በመድረኩ መግቢያ ላይ ለአባላቱ መልዕክት ያስተላለፉት በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በብዙ ውጣ ውረድ፣ ቅንጅታዊ አሠራሮች እና መስዕዋትነት ክልሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ መመለሱን ተናግረዋል። ከብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ በኃላ በርካታ አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎች ተቀምጠዋል፤ እነሱን ተግባራዊ ለማድረግ በትጋት ሥንሠራ ቆይተናል፣ እየሠራንም ነው ብለዋል።
ጥራት ባለው አስተሳሰብ፣ በዕውቀት፣ በክህሎት እና በቴክኖሎጅ ሕዝብን አቀናጅቶ የሚመራ መሪ ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል። በዛሬው የግምገማ መድረክ የመሪዎችን የአመለካከት እና የተግባር አንድነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ጥልቅ ውይይት እንደሚካሄድም ገልጸዋል።
ይህም መሪዎች በጋራ በመቆም ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በጥናት ላይ የተመሠረተ እና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል። መሪ በሥነ ምግባር መመራት አለበት ያሉት አቶ ይርጋ የመሪ ጥራትን ማምጣት ተቀዳሚ ተግባር መኾኑንም አመላክተዋል።
በዛሬው መድረክ የፓርቲው እና የመንግሥት ዕቅድ አፈጻጸሞች ይገመገማሉ፣ ጠንካራ ሥራዎች በተሞክሮነት ይያዛሉ፤ ውስንነቶችን ለመቅረፍም ልዩ አቅጣጫ ይቀመጣል ብለዋል አቶ ይርጋ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!