
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ሥብሠባውን አካሂዷል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን አንስተዋል፡፡ የባሕር በር ጥያቄን ማንሳት ነውር መኾን አክትሟል ነው ያሉት፡፡ ከማንም ጋር ስንነጋገር ትክክል ነው፣ በዓለም ላይ የእናንተን ያክል ቁጥር ኖሮት፣ ትልቅ ሀገር ኾኖ የባሕር በር የሌለው ሀገር የለም፣ ነገር ግን በውይይት እና በንግግር በሰጥቶ መቀበል መርህ መኾን አለበት፣ ግጭት እንዳትገቡ ይላሉ እንጂ የባሕር በር አያስፈልግም የሚል የለም ነው ያሉት፡፡ ይሄ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ስለ ዓባይም፣ ስለ ቀይ ባሕርም መነጋገር፣ አብሮ መሥራት ይቻላል፤ ዓባይንም ቀይ ባሕርንም እንደ ጋራ ሀብትነት መጠቀም ይቻላል የሚለው እሳቤ ግልጽ ኾኗል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ጥያቄ ያነሳው ለፖለቲካ ትርፍ አለመኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የቀይ ባሕር ሀብት በቂ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት ሲሉ በአንክሮ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላት ፍላጎት መነጋገር ነው ብለዋል፡፡ ሰጥቶ በመቀበል መርህ፣ ሕዝብን በሚጠቅም መርህ እንጠቀም እንጂ እንዋጋ አለመኾኑን ገልጸዋል፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ምስኪን፣ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ መለወጥ የሚፈልግ ሕዝብ ነው፣ የሚያስፈልገው ልማት እንጂ ውጊያ አይደለም፣ የሚያስፈልገው ተባብረን መሥራት እና ማደግ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሊፈጽም እና ከጀመርነው ሕልም ሊያስቆመን ይችላል የሚል ስጋት የለብንም ነው ያሉት፡፡ ማንም ደፍሮ አይሞክረንም፣ በቂ ዝግጅት ስላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምንዘጋጀው ውጊያ ለማስቀረት ስለኾነ በእኛ ፍላጎት ከማንም ጋር የመዋጋት ፍላጎት የለም ብለዋል፡፡
በአካባቢያችን ሰላም እና ልማት እንዲመጣ እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡ ምንም አይነት ትንኮሳ መኖር የለበትም፣ ትንኮሳ ካለ ምላሹ የከፋ እንደሚኾንም አስገንዝበዋል፡፡ በእኛ ወገን ምንም አይነት ትንኮሳ እንደማይኖር እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡ የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ብልጽግና ኖረ አልኖረ፣ ምክር ቤቱ ኖረ አልኖረ፣ መለወጥ እና ከድህነት መውጣት የሚፈልግ ሕዝብ ጫፍ ጫፉ ተሰምሮለት እስር ቤት ሊቀመጥ አይችልም ነው ያሉት፡፡
ሰላም ወዳድ ነኝ የሚል ማንኛውም አካል ከወንድሞቻችን ጋር አነጋግሮን በሕግ አግባብ የኢትዮጵያ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል፡፡ ቀይ ባሕር ሕልም ብቻ አለመኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላም እና ልማት የሚጓጉ ሰዎች ለሰላም እና ለውይይት እንዲዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!