
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ምላሽ እና ማብራሪያም ሰጥተዋል፡፡
ግጭትን ለማስቀረት ብዙ ጥናት እና ምርምር ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ማስቆም አለመቻሉን ግን ተናግረዋል፡፡ ሰላም እጅግ ውድ ዋጋ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው መንግሥት ሰላምን ያስቀደመ መኾን መቻል አለበትም ብለዋል፡፡ ሰላም የሚያደፈርስ ነገር ሲፈጠርም ዝም ብሎ ወደ ውጊያ አይገባም መመዘኛ ያስፈልገዋል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም መብት ያለው አካል ስለኾነ ለዘላቂ ሰላም ሲል ይዋጋልም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓይነት የፖለቲካ ስብራቶች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደኛው ነባሩ የመጠፋፋት ባሕል ነው ብለዋል፡፡ አዲስ መንግሥት ሲመጣ እናፍርሰው የሚል ባሕልም አለ ነው ያሉት፡፡ ሁለተኛው ከሶሻሊስት እሳቤ ጋር ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሽታ ነው ብለዋል፡፡ ይህ በሽታ ኢትዮጵያ ውስጥ የፍረጃ በሽታን ይዞ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
የሶሻሊስት እሳቤ በጽሑፍ እና በንግግር ከማመን ይልቅ በግጭት ችግሮችን ለመፍታት መነሳትን ማምጣቱን ነው የገለጹት፡፡ የፍረጃ ችግር አሁንም ድረስ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡ በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ለማፍረስ አራት ኪሎ እንገባለን የሚል ሃሳብ ተራ ልምምድ ኾኗል ነው ያሉት፡፡
“ነውጠኛ ነጻ አውጭ ነን ባዮች መጀመሪያ ተጎጂ የሚያደርጉት የራሳቸውን ሕዝብ ነው” ብለዋል፡፡ ስለምንታገልልህ እንገድለሃለን፣ እናግትሃለን እኛ ታጋዮች ስለኾን የምናደርገው ሁሉ ትክክል ነው ይሉታል ነው ያሉት፡፡ ለአማራ እና ለኦሮሞ ሕዝብ ሲባል ተነስቻለሁ የሚል ነውጠኛ መልሶ የራሱን ሕዝብ የሚገድል ከኾነ ተስፋ የለውም ብለዋል፡፡ መንግሥት ችግሮችን ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡ በሰላማዊ ውይይቶች በርካታ ታጣቂዎችን እያስገባ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የሃሳብ ነጻነት መኖሩንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ የሃሳብ ነጻነትን ሽፋን በማድረግ ችግሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ በየመድረኩ ሰላም ሰላም የምንለው የሰላምን ዋጋ ስለምናውቅ ነው ብለዋል፡፡ ጦርነት እንደማይጠቅም በወሬ ሳይኾን በተግባር አይተነዋል ነው ያሉት፡፡ ችግሮችን በውይይት እና በምክክር መፍታት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ነጻነትን እና ዲሞክራሲን የማሥተዳደር ችግር መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ሁልጊዜም ችግሮችን በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት ለብዙዎች ሰላምን የሚሰጥ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ስምምነቱን ያደረገው ባሸነፈው ጦርነት ነው፣ ይሄን ያደረገ ኃይል የለም፣ ስምምነቱም ለውጥ አምጥቷል ነው ያሉት፡፡
በፕሪቶሪያ ስምምነት አማካኝነት ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና መልሶ የማቋቋም ሥራው በተሟላ መንገድ እየተፈጸመ አይደለም ብለዋል፡፡ መንግሥት በስምምነቱ መሠረት ሥራዎችን ለመፈጸም ዝግጁ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የሚፈልገው ሰላም ነው ብለዋል፡፡ በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ መከላከያ ተወጥሯል ጦርነት እናንሳ የሚሉ አሉ፤ ምክሬ ግን አያዋጣም፣ አይኾንም ተውት የሚል ነው ብለዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!