
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 6ኛው ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 21ኛ መደበኛ ሥብሠባውን እያካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት ስምንት ወራት በሀገር ውስጥ ለ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
300 ሺህ ለሚኾኑት ደግሞ የውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል የተፈጠረ መኾኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 45 ሺህ የሚኾኑት ዜጎች ደግሞ በሀገር ውስጥ እየኖሩ ከውጭ ድርጅቶች ጋር በመሥራት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ኾነዋል ብለዋል።
የሥራ ፈላጊው ቁጥር ከፍተኛ ቢኾንም ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የተፈጠረው የሥራ ዕድል ግን አበረታች ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። በተለይም የሀገር ውስጥ የሥራ የዕድል ፈጠራን የተሸከሙት ግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፎች መኾናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብርና 40 በመቶ፣ አገልግሎት 38 በመቶ እና ኢንዱስትሪ 20 በመቶ የሥራ ዕድል ፈጠራውን ሸፍነዋል ሲሉ አስረድተዋል።
በተለይም ደግሞ የኮሪደር ልማት እና ልዩ ልዩ የለውጥ ተግባራት ቀን እና ሌሊት በመሥራት በርካቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ስለማድረጋቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ደመወዝ የቆየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!