
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ሥብሰባውን እያካሄደ ነው፡፡
በምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጉዳዮች ምላሽ እና ማብራሪያም ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በትራንስፖርት ከአፍሪካ በቀዳሚነት እንደምትቀመጥ አንስተዋል፡፡ የአየር እና የመዳረሻ ቦታዎችን ቁጥር በማሳደግ፣ አዳዲስ አየር መንገዶችን ገንብቶ ሥራ በማስጀመር እና የበረራ ድግግሞሽን በማሳደግ ከፍተኛ ገቢ ማግኘቷን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በአፍሪካ ትልቁን አየር መንገድ ለመገንባት ሥራ መጀመሯን አንስተዋል፡፡ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የዲዛይን ሥራ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ ሀገሪቱ በቀጣይ ለመገንባት ካቀደቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ያደርገዋልም ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ባሕር ኀይል ተጨማሪ መርኮቦችን በማስገባት እና ሥራውን በማዘመን ትርፋማነቱን ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የባቡር ትራንስፖርት ዘርፉ ከባለፉት ዓመታት እየተሻሻለ መጥቷል፤ የዲጅታል ግብይት መቶ በመቶ አድጓል፡፡ የፋይናንስ ተቋማትም በከፍተኛ ኹኔታ ዕድገት እያሳዩ መኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወዳዳሪነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ መሠባሠብ እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡
በዚህ ዓመት ከ80 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በማካሔድ የቱሪዝም ዕድገቱን ማነቃቃት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ካሳዩ ሀገራት በቀዳሚነት እንደምትጠቀስም ነው የገለጹት፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ እንዲያድግ መንግሥት ከቀበሌ ጀምሮ አገልግሎቱን ለማጠናከር በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባለፈ አገልግቶችን በአንድ ማዕከል መስጠት የሚያስችል የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመተግበር እየተሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!