
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች አሥተዳደር የኢንቨስትመንት ሆልዲንግን ለማቋቋም ባሥጠናው ጥናት ላይ ውይይት አድርጓል። በውይይቱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)ን ጨምሮ የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች እና የልማት ድርጅት መሪዎች ተገኝተዋል።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ የልማት ድርጅቶች የልማት ክፍተትን በመሙላት፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና ሌሎች የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በመከወን በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በአንጻሩ በኪሳራ፣ በሥራ ሽሚያ እና በሌሎችም ችግሮች ከክልሉ ሕዝብ የልማት ፍላጎት ውጭ የኾኑ ድርጅቶች እንዳሉም በጥናት መገኘቱን ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል። የልማት ድርጅቶቹ ለሕዝብ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በሕግ ማዕቀፍ የተካተተ እንዲኾን፣ በግልጽ የተለየ አደረጃጀት እንዲኖራቸው እና ዋናው ተልዕኳቸው ሃብት ፈጠራ እንዲኾን ባለፈው ጊዜ ጥናት ተጠንቶ በአንድ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የልማት ድርጅቶቹ በመተባበር በትልቅ ገበያ ተወዳድረው አሸናፊ እንዲኾኑ በገበያ የሚመራ ሥርዓትን የሚመጥኑ እንዲኾኑ ማድረግ አስፈልጓል ነው ያሉት። ትርፍን በማሳደግ እና ማኅበራዊ ኀላፊነትን መወጣት እና ግልጽ ያልኾኑ ዓላማዎቻቸውን ለይተው እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የድርጅቶቹ መሪዎች በዘርፉ ዕውቀት እና ክህሎት ባለው መንገድ በግልጽነት እንዲመሩ በማድረግም በትርፋማነት እንዲሠሩ የማድረግን አስፈላጊነት አንስተዋል።
የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በማቋቋም ድርጅቶቹ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ በመኾን አማራ ክልል እያጋጠሙት ያሉትን የምጣኔ ሃብት ችግሮች ለመቅረፍም እንደሚያስችል ተናግረዋል። በሌሎች ዘርፎችም የማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድሩ የልማት ድርጅቶችን ወደ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የማሻሻል ጉዳይም የምጣኔ ሃብቱ ማሻሻያ ሥራ አንዱ አካል መኾኑን ገልጸዋል።
ከቀጥታ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ ለመኾን እና ከትርፋቸው ለሕዝብ ልማት የሚያግዙበት ሁኔታን ለማጠናከር ድርጅቶቹ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ በመኾን ክልሉን የሚጠቅሙ እንዲኾኑ ግልጽ ተልዕኮ፣ ግልጽ አሠራር እና ተጠያቂነት ባለው መንገድ ይዘው እንድንቀሳቀሱ በኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የማደራጀቱን አስፈላጊነት አንስተዋል።
የልማት ድርጅቶቹም የማሻሻያ ዕቅዶቻቸውን መከለስ እንደሚያስፈልጋቸው አመላክተዋል። በተደረገው ጥናትም የክልሉ የልማት ድርጅቶች በአንድ የተጠናከረ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጥላ ሥር ቢመሩ የበለጠ ውጤታማ ያደርጋቸዋል ብሎ ክልሉ ማመኑን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!