“ባለፉት ስምንት ወራት ከ580 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠብሥቧል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር)

27

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ሥብሠባውን እያካሄደ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያም ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸው ባለፉት ስምንት ወራት ከ580 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠብሥቧል ብለዋል፡፡ የተሠበሠበው ገቢ ጥሩ የሚባል ቢኾንም ከድጎማ እና ከሌሎች ወጭዎች አንጻር አሁንም ወጭው ከፍ ያለ መኾኑን አንሰተዋል፡፡

ገቢ ካልተሠበሠበ በስተቀር የልማት ጥያቄዎች አይመለሱም ነው ያሉት፡፡ የተሠበሠበው ገቢ ጥሩ ቢኾንም የተሻለ ገቢ መሠብሠብ ይገባል ብለዋል፡፡ በተደረገ የዕዳ ሽግሽግ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ኢትዮጵያ አትርፋለች ነው ያሉት፡፡ የተደረገው ድርድር ፍሬ አግኝቷልም ነው ያሉት፡፡ ይሄም በዕዳ ቅነሳ ላይ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አቋም እዳ እንዲሰረዝ ማድረግ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት ያገኘችው የውጭ ገበያ ከየትኛውም ዓመት ይበልጣል ብለዋል፡፡ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ለውጭ ገበያ ማቅረቧንም ነው የተናገሩት፡፡ በሚቀጥሉት አራት ወራት አኹን ባለው ሂደት ከቀጠለ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ስኬት ይመዘገባል ነው ያሉት፡፡

የዋጋ ንረትን ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የዋጋ ግሽበትን መቀነስ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡ የምርት መጨመር፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ሌሎች ሥራዎች የዋጋ ንረቱን መቀነሱንም ገልጸዋል፡፡ የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት መቀነስ አንድ እና ያው አለመኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የዋጋ ግሽበት እንዳይጋነን መቆጣጠር እና የሰውን ገቢ ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ተጎጂ እንዳይኾኑ የደመወዝ ጭማሪ መደረጉንም አንስተዋል፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖችን ከጫና ለማውጣትም በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article‘’የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እምርታዊ ለውጥ አስመዝግቧል’’ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየአማራ ክልል መንግሥት የልማት ድርጅቶችን በኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሊያቋቁም ነው።