‘’የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እምርታዊ ለውጥ አስመዝግቧል’’ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

27

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 6ኛው ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 21ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያሄደ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በሠጡት ማብራሪያ መንግሥት በ10 ዓመታት የሚተገበር የልማት እቅድ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የ8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበች መኾኗን ለአብነት ጠቅሰዋል። በዚህ ዓመትም የ8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የኢኮኖሚ እድገቱ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን መሠረት ያደረገ መኾኑን ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት አኳያ ሲታይ በእጥፍ እድገት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።

በተለይም እድገት ከተመዘገበባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች መካካል ግብርና ትልቅ እምርታ እንዳስመዘገበ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የግብርና ሥራ በአብዛኛው የሚከወነው አነስተኛ እና መካከለናኛ የመሬት ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች መኾኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ብቻ በአነስተኛ ባለይዞታ የተሸፈነ ሰብል ከ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ወደ 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መድረሱን አስረድተዋል።

በኩታ ገጠም ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ወደ 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬትም በሰብል በመሸፈን እምርታዊ እድገት አስመዝግቧል ብለዋል። በሰብል ልማት ለውጥ ከታየባቸው ሥራዎች መካከል የስንዴን ምርታማነት ያህል አድገት ያስመዘገበ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመኸር እና በመስኖ በስንዴ ከተሸፈነው 7 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ደረጃ ያዘች ስንዴ አምራች ሀገር አድርጓታል ብለዋል። ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የሰጡበት ጉዳይ በቡና ምርት እና ምርታማነት ላይ ነው። ከቡና ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እያደገ መጣቱን አብራርተዋል።

በለውጡ ማግስት ከቡና ኤክስፖርት 700 ሚሊዮን ዶር እንደማይበልጥ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት 8 ወራት ብቻ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ከቡና ኤክስፖርት መገኘቱን ተናግረዋል። የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን የበለጠ በማጠናከር እና በማስፋት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ የበለጠ ማሳደግ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የዕዳዳ ሸግሽግ መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ።
Next article“ባለፉት ስምንት ወራት ከ580 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠብሥቧል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር)