“በዚህ ዓመት ብቻ ከ55 በላይ አዳዲስ ፋብሪካዎች ሥራ ጀምረዋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

13

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ሥብሥባውን እያካሄደ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያም ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸው ባለፉት ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፉ እንዲያድግ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ፈተና እንደነበር የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን ለመፍታት ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡

የኢንዱስትሪዎችን የኀይል አቅርቦት ለመፍታትም መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ የቀረበው ኀይል ከአምናው በ50 በመቶ መጨመሩንም ተናግረዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ 47 በመቶ ኀይል ጨምሯል ነው ያሉት፡፡ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የጨመረው ኀይል ከፍ ያለ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ያለው ፍላጎት ሌሎች ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግም አመለካች ነው ብለዋል፡፡

ብረትን አቅልጦ ለኢትዮጵያ ልማት ለማዋል ጥሩ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡ ለልማት የሚውሉ ብረቶችን ለማምረት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯልም ነው ያሉት፡፡ የሲሚንቶ አቅርቦትን ለመጨመር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የመስታውት ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡

በሴራሚክ፣ በግራናይት እና በማርብል ያለው አቅም ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ አቅሞችን አቀናጅቶ መጠቀም ከተቻለ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ያድጋል ነው ያሉት፡፡ የማምረት አቅም ከ47 በመቶ ወደ 61 በመቶ ማደጉንም አስታውቀዋል፡፡ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት ትልቅ ነው ነገር ግን አኹንም ሥራ ያስፈልገዋል፤ ከዚህ በላይም ማደግ አለበት ነው ያሉት፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ ከ55 በላይ አዳዲስ ፋብሪካዎች ሥራ ጀምረዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ120 በላይ ፋብሪካዎች አዲስ ፈቃድ ስለማውጣቸው አብራርተዋል፡፡ እየተሠራ ካለው ሥራ አንጻር ኢንዱስትሪው በዚህ ዓመት የተቀመጠለትን ግብ እንደሚያሳካ ሙሉ ዕምነት እንዳላቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየምክር ቤት አባላቱ በሰላም ጥሪዎች እና በኑሮ ውድነት ላይ አተኩረው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
Next articleበአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የ8 ወራት የሥራ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።