
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት በ6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ሥብሠባውን አካሂዷል። የምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ እያጋጠሟት ስላሉት ወቅታዊ ጉዳዮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አቅርበዋል።
የምክር ቤት አባላቱ ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ዋነኞቹ የፖለቲካዊ መፍትሔዎች አስፈላጊነት፣ የሰላም ጥሪዎች፣ የኑሮ ውድነት፣ የሕግ የበላይነት እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅታዊ ሁኔታ ይገኙበታል። የምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ እያጋጠሟት ላሉት ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ጥሪዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ሁሉም አካላት ለሰላም እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም የኑሮ ውድነት በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መኾኑን እና መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥበት አባላቱ አሳስበዋል።
የፍትሕ ሥርዓቱ ችግሮች እንዳሉበት እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥም ጠይቀዋል።
ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅታዊ ሁኔታ እና ቀሪ የግንባታ ጊዜ ላይ የምክር ቤት አባላት ጥያቄ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በምክር ቤቱ ለተነሱት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ የሰጡ ሲኾን መንግሥት በሁሉም ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!