
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 6ኛው ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ሥብሠባውን እያካሄደ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን እና አስተያየት እያቀረቡ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት እየተነሱ ላሉ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡
የምክር ቤት አባላቱ እንደ ሀገር የሚበረታቱ እና ሊሰፉ የሚገባቸው መልካም ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጠንካራ መንግሥት ጠንካራ መገለጫዎች የኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ዘመን ተሻጋሪ እና ትውልድ የሚኮራባቸው ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም አንስዋል፡፡
እንደ ሀገር ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን በውይይት እና በድርድር የመፍታት ልምምዳችን አነስተኛ ነው ያሉት አባላቱ መገዳደል እና መጠፋፋት ዛሬም ዋጋ እያስከፈለ ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያብራራ ጠይቀዋል፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት እና አፈጻጸም ብሎም አተገባበር ያለበትን ደረጃም ጠይቀዋል፡፡
በሕዝብ ዘንድ የሚነሱ የፍትሕ እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የሚበራታቱ ቢኾንም አሁንም የፍትሕ ተደራሽነት ችግሮች እና የመልካም አሥተዳደር እጦት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ መንግሥት በፍትሕ ሥርዓቱ እና በመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች እንዲብራሩላቸውም ጠይቀዋል፡፡
የሕግ የበላይነት እንዲከበር እየተሠራው ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው ያሉት አባላቱ ነገር ግን ዛሬም ቢኾን በአክራሪዎች፣ በጽንፈኞች እና በታጣቂዎች የሚገደሉ ዜጎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ የሚታገቱ እና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጸምባቸው በርካቶች መኾናቸውንም አንስዋል፡፡ ይሄን የሰላም ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን እየተሠራ እንደኾነ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት ጫካ ከገቡ አካላት ጋር ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እየሠራው ያለው ሥራ የሚበረታታ ቢኾንም አሁንም ችግሮች አሉ ነው ያሉት፡፡ መንግሥት የጸጥታ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት እየሠራቸው ያሉ ሥራዎችም እንዲብራሩላቸው አንስተዋል፡፡
መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረጉ ምክንያት የሚከሰቱ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም ድጎማ እያደረገበት ያለው መንገድ ምሥጋና የሚቸረው ነው ብለዋል፡፡ ይህ ርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡ መንግሥት ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በመቋቋም የሚያቀርበው ነዳጅ ገበያው እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነትን እያባባሰ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ኾኗል ነው ያሉት፡፡ የነዳጅ ምርት በየወሩ እየጨመረ መምጣቱ ምክንያቱ እንዲብራራም ነው የጠየቁት፡፡
ሕገ ወጥነትን ለመከላከል እየተሠራ ያለው ሥራ ምን እንደኾነም ይብራራ ነው ያሉት፡፡ እንደ ሀገር የዋጋ ንረትን እና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የምግብ ዋጋ ግሽበት መቀነሱ ሪፖርት ቀርቧል ያሉት የምክር ቤቱ አባላት ነገር ግን የመንግሥት ሠራተኞች እና ሌሎች በኑሮ ውድነት እየተቸገሩ ባለበት ወቅት እንዴት እንዲህ ተብሎ ሊቀርብ ቻለ፣ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ምን ያክል የተቀራራበ ነው ብለዋል በጥያቄያቸው፡፡
የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል ያሉት አባላቱ ለሰላም ቆራጥ በመኾን የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡ በአማራ ክልል በገጠር አካባቢዎች ትምህርት የለም፤ መሪዎች ይገደላሉ፣ ግጭቶችም ቀጥለዋል ብለዋል፡፡ በሰሜኑ ያለውን ችግር የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ማስተካከል አለበት ብለዋል፡፡
የኮሪደር እና ሌሎች የልማት ሥራዎች የሚበረታቱ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!