
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ አካሂደዋል። መድረኩ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ እና መሠረተ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ ( ዶ.ር) ገልጸዋል።
በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ የከተማ ልማት ተቋማት ያጋጠሟቸውን ውስንነቶች በመቋቋም ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወናቸውን መድረኩ አረጋግጧል ነው ያሉት ዶክተር አሕመዲን መሐመድ። በቀጣይ አራት ወራት ውስጥ ከክልል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የተቀናጀ እና የተጠናከረ የትግበራ እንቅስቃሴ በማድረግ የታቀዱትን ግቦች ለማሳካት የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧልም ብለዋል።
በተለይም መልካም አሥተዳደርን በማስፈን እና ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ላይ ልዩ ትኩረት ስለመሰጠቱም አብራርተዋል። የተቋማትን አቅም በመገንባት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ ዋና ዋና ተግባራትን በማከናወን እና በሀገር አቀፍ ተነሳሽነቶች ላይ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የመስክ ድጋፍ፣ ክትትል እና የሱፐርቪዥን ሥራዎች ወደ ዞኖች እና ከተሞች በስፋት እንዲወርዱ ተወስኗል ብለዋል።
መድረኩ የተቋማቱን አቅም በማጠናከር ለኅብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ስለመኾኑም ነው የተገለጸው። የግምገማ መድረኩ የተቋማቱን አፈጻጸም ለማሻሻል እና ለቀጣይ ስኬት ጠንካራ መሠረት ለመጣል ያለመ መኾኑንም ነው ዶክተር አሕመዲን መሐመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ያሰፈሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!