
ሁመራ: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በጤና ሚኒስቴር እና በአማራ ክልል የጤና ተቋማት ትብብር ቀጣናዊ አገልግሎት መስጠት የሚችል ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የጤና ላቦራቶሪ በሁመራ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ እየተገነባ መኾኑ ተገልጿል።
ላቦራቶሪው ባለ ሁለት ወለል እና ከ36 በላይ አጠቃላይ ክፍሎች ያሉት ሲኾን በ1 ዓመት ከ6 ወር ለማጠናቀቅ እቅድ እንደተያዘ የፕሮጀክቱ ማናጀር ኢንጂነር ዓሊ ታመነ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ የሥራ ሰዓትን እና ሠራተኛ በመጨመር በስድስት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሠራ ነው ሲሉ ኢንጅነሩ ገልጸዋል።
ላቦራቶሪውን የጤና ሚኒስቴር ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመኾን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ እያስገነባው ይገኛል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሰው ኃይል መልምሎ በማሰማራት የድርሻውን እያበረከተ መኾኑ ተጠቁሟል። የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም በተባባሪነት ግንባታውን እየደገፈ መኾኑን ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ላቦራቶሪው በአካባቢው እንዲገነባ የታቀደበት ዓላማ በአጎራባች ሀገራት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ጉዳት እንዳያደርሱ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲቻል ነው ሲሉ የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ስማቸው ግደይ አብራርተዋል። ላቦራቶሪው ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር በተጨማሪ ከሁመራ አጠቃላይ ሆስፒታል አቅም ውጭ የኾኑ የጤና እክሎች ሲያጋጥሙ ወደ ጎንደር፣ ባሕር ዳር እና አዲስ አበባ በመላክ ይገጥም የነበረውን እንግልት እንደሚያስቀር ኀላፊው ገልጸዋል።
ለተከሰቱ በሽታዎች ምላሽ ከመስጠት ባሻገርም አዳዲስ ጥናቶችን በማድረግ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ፋይዳ ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ እየተገባ እንዲሚገኝም አቶ ስማቸው አስረድተዋል። ላቦራቶሪው ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ባሻገር ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ያሉት በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ናቸው።
ጤና ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ግንባታውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እያደረጉት ያለው ትጋት የሚደነቅ ነው ብለዋል። የሁመራ አጠቃላይ ሆስፒታል ለረጅም ጊዜ በርካታ አገልግሎቶችን እየሰጠ ቢኾንም በጥገና እና በዘመናዊ መሳሪያዎች መታገዝ ቢችል የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል አሥተዳዳሪው ጠቁመዋል።
ይሄንን ለማድረግም በጤናው ዘርፍ ላይ አሻራቸውን ማኖር የሚፈልጉ ተቋማት የሙያ፣ የቁሳቁስ እና የመድኃኒት እገዛዎችን ማድረግ ቢፈልጉ የዞኑ አሥተዳደር የማይቋረጥ ድጋፍ እንደሚሰጣቸው አስገንዝበዋል። ለሁሉም ልማቶች የሰላም ዋጋ ከፍተኛ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው የጤናውን ዘርፍ ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን በተፈለገው ሁኔታ ለማጠናቀቅ እና የኅብረተሰቡን አገልግሎት ለማቀላጠፍ የዞኑ አመራር ጠንክሮ እየሠራ ነው ብለዋል።
የክልሉ እና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በመገንባት ላይ ያለውን ላብላቶሪ እና የሁመራን አጠቃላይ ሆስፒታል ነባር የላብላቶሪ ክፍሎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን