
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከሬንቦ አግሮ ሳይንስ ኬሚካል አምራች ካምፓኒ፣ ከዩኒየኖች፣ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ከተመረጡ አርሶ አደሮች ጋር በጸረ አረም አጠቃቀም እና አሥተዳደር ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) እንዳሉት ተባይ እና አረም ምርት እና ምርታማነትን ከሚቀንሱት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በሰብል ላይ የሚከሰትን ተባይ በአግባቡ መቆጣጠር ካልተቻለ ምርትን ሙሉ በሙሉ እስከ ማሳጣት እንደሚያደርስ ነው የገለጹት። ከዚህ በፊትም የተባይ ክስተትን ለመከላከል በባሕላዊ መንገድ እና ኬሚካልን በመጠቀም የቁጥጥር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የሚገቡ ኬሚካሎችን አርሶ አደሮች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከማድረግ አኳያ ችግሮች እንደነበሩ ገልጸዋል። ወደ ክልሉ የሚገቡ ኬሚካሎችን ለመከታተል እና የአርሶ አደሮችን ደኅንነት ለመጠበቅ የግብርና ጥራት ቁጥጥር ተቋም ተቋቁሞ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ወደ ክልሉ የሚገቡ ኬሚካሎችም የጎንዮሽ ጉዳታቸው ዝቅተኛ የኾኑ፣ ምርታማነትን የሚያሳድጉ፣ የተሻለ ተባይ የመከላከል አቅም ያላቸው እና የአርሶ አደሩን የምጣኔ ሃብት አቅም ያገናዘቡ ሊኾኑ ይገባል ብለዋል። የተሻለ የኬሚካል አቅርቦት እንዲኖር እና በአጠቃቀም ችግር ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና የክልሉ ግብርና ቢሮ በተቀናጀ መንገድ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን