
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ እና የሚጠበቀው ምርት እንዲገኝ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ለአርሶ አደሮች ማድረስ ይገባል። ከዚህ አኳያ አርሶ አደሩ በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ማዳበሪያ እንዲደርሰው ታሳቢ ያደረገ ሥራ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተሠራ ነው የሚገኘው።
ፍትሐዊ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እንዲኖር እየሠሩ ከሚገኙ አካባቢዎች መካከል የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ይገኝበታል። ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ማዳበሪያ እንዲሰራጭ የተሻለ ሥራ ለመሥራትም ዩኒየኖችን እየተጠቀመ ነው። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የአድማስ ዩኒየን ግብዓት አቅርቦት ስርጭት እና የኢንዱስትሪ ምርት ግብይት ክፍል ኀላፊ ቢተው መኮንን በበጀት ዓመቱ 856 ሺህ 660 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በማስገባት ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት በማቀድ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡
ዩኒየኑ እስካሁን 235 ሺህ 778 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ያስገባ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው 127 ሺህ 656 ኩንታል ወደ መሠረታዊ ማኅበራት ማሰራጨታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ስርጭቱ ከነጋዴ እና ደላላ ነጻ ኾኖ በፍትሐዊነት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ከባለድርሻ አካላት እና ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በንቅናቄ መድረክ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ተናግረዋል፡፡
ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ግብዓቶችን በወቅቱ ለማሰራጨት እና ፍትሐዊ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡ ለዚህም 856 ሺህ 660 ኩንታል የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አዲሱ ስማቸው ተናግረዋል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ 216 ሺህ 722 ኩንታል ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በአራት ማዕከላት ገብቷል፡፡ 118ሺህ 126 ኩንታል የሚኾነው ወደ መሠረታዊ ማኅበራት መሠራጨቱንም ነው ምክትል ኀላፊው የተናገሩ፡፡ ይህንን የአፈር ማዳበሪያ በፍትሐዊነት እና በወቅቱ ለማሰራጨት የግብርና ባለሙያዎች ከሚመለከታቸው የቀበሌ ባለሙያዎች ጋር በመኾን ሰፊ የኤክስቴንሽን ሥራ ሠርተዋል፡፡
በዚህም የየአንዳንዱ አርሶ አደር መሬት እና ሰብል ታሳቢ ያደረገ ቅድመ ጥናት በማድረግ እራሱን የቻለ የግብዓት ስርጭት አሥተባባሪ ኮሚቴ በማዋቀር፣ በመተቸት እና በመገምገም ስርጭቱ እየተከወነ ነው፡፡ በሥራ መካከል ሕገወጥ የኾነ እንቅስቃሴ ሊኖር እንደሚችል የገለጹት ምክትል ኀላፊው ይህንን ለመከላከል ከባለፈው ዓመት እና ከዛም በፊት የነበረውን ጉድለቶች በመገምገም ክፍተቶችን ለማስተካከል ጥረት ተደርጓል፡፡
ከዚህ በፊት ኬላዎችን በመዘርጋት ሕገ ወጥ የኾነ የአፈር ማዳበሪያ ከወረዳ ወረዳ እና ከቀበሌ ቀበሌ ባልተገባ መንገድ እንዳይንቀሳቀስ ቁጥጥር የማድረግ ሥራም እየተሠራ ስለመኾኑ ጠቁመዋል። ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ2017/18 የምርት ዘመን 407 ሺህ 026 ሄክታር መሬት ለማልማት አቅዶ እየሠራ መኾኑንም ነው ምክትል ኀላፊው የገለጹት፡፡
ክልሉ ምርት እና ምርታማነትን ውጤታማ ለማድረግ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ መኾኑን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ችግር እንዳይፈጠር ከክልል እስከ ገጠር ቀበሌ ድረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባባት ላይ ተደርሷልም ብለዋል፡፡
ዶክተር ድረስ ምርት እና ምርታማነት እንዲረጋገጥ የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሮች ላይ በትክክል መድረሱን ማረጋገጥ እንደሚገባም ነው የተናገሩት። የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ላይ በእጅ አዙር እንዳይደርስ እና መድረስ የሌለበት አካል ላይ እንዳይደርስ ዩኒየኖች በትክክል ሥራዎችን እንዲሠሩ እየተሠራም ስለመኾኑ ነው ያስገነዘቡት።
የግብርና መዋቅሩ በማዳበሪያ ሥርጭት ላይ የሚዝል አቅም እንደሌለው ያስረዱት ዶክተር ድረስ ይህም እንዲኾን በየጊዜው እየተገመገመ እየተመራ ስለመኾኑ ነው ያስገነዘቡት። ሁሉም ዞኖች እስከ ቀበሌ ድረስ በወረደ አግባብ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭቱን የሚቆጣጠር ግብረኃይል አቋቁሞ እየሠራ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
የአፈር ማዳበሪያ በሕገወጥ መንገድ እንዳይንቀሳቀስ ከዞን እስከ ቀበሌ መቆጣጠሪያ ኬላ እንዲኖር እና አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግ መግባባት ላይ ተደርሶ ተግባራዊ እየተደረገ ያለበት ኹኔታ እንዳለም ነው የጠቆሙት።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!