
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከሬንቦ አግሮ ሳይንስ ኬሚካል አምራች ካምፓኒ፣ ከዩኒየኖች፣ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ከተመረጡ አርሶ አደሮች ጋር በጸረ አረም አጠቃቀም እና አሥተዳደር ዙሪያ ውይይት አድርጓል። የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ክፍሌ ወልደ ማርያም እንዳሉት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ለማቅረብ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል።
ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ደግሞ መሬትን አለስልሶ ከማረስ ጀምሮ የተሟላ የግብርና ቴክኖሎጂን መጠቀም ያስፈልጋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች፣ የአፈር ማዳበሪያዎች እና በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር እና በግብርና ባለሥልጣን የተረጋገጡ ጸረ አረም እና ጸረ ተባይ ኬሚካሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታወቁ ተቋማት በማስገባት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
አኹን ላይም የሬንቦው ምርት የኾኑት ጸረ አረም እና ጸረ ተባይ ኬሚካሎች በጥናት ተረጋግጠው እና ተመዝግበው በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አማካኝነት ለአርሶ አደሮች እንዲቀርቡ ተደርጓል ብለዋል። ኮርፖሬሽኑ በቀጥታ ከድርጅቱ ተረክቦ ስለሚያቀርብ አርሶ አደሮችን ከተጨማሪ ወጭ ከማዳኑ ባለፈ በወቅቱ ግብዓቱን እንዲያገኙ ያደርጋልም ነው ያሉት።
አርሶ አደሮች ትክክለኛውን የጸረ አረም እና የጸረ ተባይ ኬሚካሎች በወቅቱ ገዝተው በተገቢው መንገድ እንዲጠቀሙም አሳስበዋል። የሬንቦ አግሮ ሳይንስ ኬሚካል አምራች ካምፓኒ ዋና ሥራ አሥኪያጅ አሸናፊ አለማየሁ እንዳሉት ካምፓኒው በግብርና ሚኒስቴር የተረጋገጡ ጥራት ያላቸው ጸረ አረም፣ ጸረ ተባይ እና ጸረ በሽታ ኬሚካሎችን በማምረት እያቀረበ ይገኛል።
ምርቱ በኮርፖሬሽኑ በተመጣጣኝ ዋጋ በቀጥታ ለአርሶ አደሮች ስለሚደርስ አርሶ አደሮችን ከአላስፈላጊ ወጭ እንደሚታደግም ነው የገለጹት። ኬሚካሎች ሊያደርሱት የሚችሉትን የጎንዮሽ ጉዳት ለመቀነስ ዓለም አቀፍ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ባስቀመጠው የጥራት ቁጥጥር ዘዴ መሠረት የተመሠረላቸው ናቸው ብለዋል።
በአጠቃቀም ወቅት ደግሞ በሰው፣ እንስሳት እና በሌሎች አካላት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለአርሶ አደሮች በሠርቶ ማሳያዎች እና የአርሶ አደሮችን ቀን እና መድረኮችን በማዘጋጀት በተግባር የተደገፈ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ ነው የገለጹት። የአድማስ ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒዬን የቦርድ ሰብሳቢ አርሶ አደር ተስፋዬ አዲስ እንዳሉት የግብርና ግብዓት በተገቢው መንገድ በመጠቀማቸው ከእጥፍ በላይ የምርት ጭማሬ እንዳገኙ ተናግረዋል።
በግብርና ባለሙያ ምክረ ሐሳብ መሠረት ጸረ አረም እና ጸረ ተባይ ኬሚካል መጠቀም ከተቻለ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የአካባቢን ደኅንነት መጠበቅ እንደሚቻል ባለፉት ዓመታት ተሞክሮ መውሰዳቸውን በግብርና የተሰማሩ ሀሳብ ሰጭዎች ተናግረዋል። ይኹን እንጅ አኹንም በግለሰብ ሱቆች የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ኬሚካሎች በመግዛት የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ነው ያነሱት።
በኬሚካል አጠቃቀም የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ሥልጠናዎችን እስከ ታች ድረስ መሥጠት እንደሚገባ መክረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን