የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) ከሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ።

14

ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) ከሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢንጂነር ዋሊድ ቢን አብዱልከሪም ኤልኬሬጂ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። በውይይታቸው በኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ተነስቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያም መክረዋል። ኢትዮጵያ ገለልተኛ አቋም የምታራምድ መኾኗንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት እና ወዳጅ ሀገር ሱዳን ያጋጠማት ችግር እንዲፈታ ወጥ በሆነ መንገድ መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

የሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢንጅነር ዋሊድ ቢን አብዱልከሪም ኤልኬሬጂ ሀገራቸው የሱዳን ቀውስ መቋጫ እንዲያገኝ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደምትሠራ ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሳዑዲው አቻቸው ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል የኢኮኖሚ ትሰስር በሚጠናከርበት መንገድ፣ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች እና ሌሎች የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመፍጠሩ የሳዑዲ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ጠይቀዋል። የሳዑዲው አቻቸው ኢንጅነር ዋሊድ ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና ዘርፍ፣ በማዕድን ፣ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ ናት ብለዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው አምባሳደር ምስጋኑ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አንድ የደኀንነት ስጋት አድርጎ ስለሚወስደው አደጋውን ለመከላከል ከሪያድ ጋር ጠንካራ ትብብር ማድረግ እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቢጃይ ኢንዱስትሪያል እና ኢንጂነሪንግ ሶሉሽን ከአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ጋር በትብብር እንደሚሠራ አስታወቀ።
Next articleበኬሚካል አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ ነው።