
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቢጃይ ኢንዱስትሪያል እና ኢንጂነሪንግ ሶሉሽን ባለቤት ኢንጅነር ቢጃይ ናይከር በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘውን የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል። አማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የተለያዩ ማሽኖችን ለማምረት አቅም ያለው ኢንዱስትሪ መኾኑን እና አንድ ሀገር ሊኖራት የሚገባ ሁነኛ ሃብት ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪው የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን፣ የግንባታ ግብዓቶችን፣ ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎችን እንዲሁም እንደ ወርቅ እና ጅብሰም ያሉ ማዕድናትን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ለመሥራት አቅም እንዳለውም ኢንጂነር ቤጃይ አረጋግጠዋል። በቡርኪናፋሶ እና በሌሎችም ሀገራት አምራች ፋብሪካዎችን ለመትከል ውል መውሰዳቸውን ጠቅሰው ከአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ጋር በቅርበት ኾነው በጋራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪው ወደ ውጭ የሚላኩ በርካታ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችል ስለመኾኑም ገልጸዋል። በውስጡ የሚሠሩ ባለሙያዎችም ልምድ እና ዕውቀት ያላቸው ስለመኾናቸው ኢንጂነር ቢጃይ ተናግረዋል። አማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና መሰል ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ኢኮኖሚ፣ ለቴክኖሎጂ ነጻነት እና ለአጠቃላይ ሀገራዊ ሉዓላዊነት ወሳኝ ናቸው ብለዋል። በመኾኑም መንግሥት የመብራት፣ የውኃ፣ የመንገድ፣ የፋይናንስ እና መሰል መሠረተ ልማቶችን በማቅረብ የበለጠ ማስፋፋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የመኪና ሞተር ዓለም ላይ የተሠራው ከመቶ ዓመታት በፊት መኾኑን ጠቅሰው እስካሁን ድረስ ግን በሀገራችን ላይ መሠራት አለመቻሉ ሊያሳስበን ይገባል ብለዋል። ያለንን ጥሬ ዕቃ በመጠቀም የሰው ኃይላችንን በማብቃት እና ጠንካራ ፓሊሲዎችን በመቅረጽ ለሀገር ኢኮኖሚ እና ደኅንነት የሚኾኑ ቴክኖሎጂዎችን በራሳችን አቅም ማምረት አለብን ሲሉም አሳስበዋል።
“የቴክኖሎጂ ጉዳይ ለነገ የሚተው አይደለም፤ ዛሬውኑ ጀምረን የምናሳድገው ለትውልድም የምናስተላልፈው መኾን አለበት” ብለዋል። ቢጃይ ኢንዱስትሪያል እና ኢንጂነሪንግ ሶሉሽን በኢትዮጵያ ብቻ ከ90 በላይ ፋብሪካዎችን አምርቶ ተክሏል ያሉት ኢንጂነሩ ይህንን የበለጠ ለማስፋት ከአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ጋር በትብብር እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል። በጋራ በመኾን በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ ፋብሪካ በመትከል ያለንን አቅም እናሳያለን፤ በመቀጠልም በስፋት በመሥራት ምርቶቻችንን ለውጭ ሀገር ገበያ እናቀርባለን ብለዋል ኢንጅነር ቢጃይ።
የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዘላለም በላይ አሁን ላይ ዘመናዊ የመብራት ፖሎችን፣ የማፋሰሻ ቦይ ክዳኖችን እና ሌሎችንም ለኮሪደር ልማት ሥራዎች የሚኾኑ ግብዓቶችን እያመረተ ነው ብለዋል። እነዚህ ግብዓቶች ቀደም ሲል ከውጭ ሀገር ይገቡ እንደነበርም አስታውሰዋል። ከቢጃይ ኢንዱስትሪያል እና ኢንጂነሪንግ ሶሉሽን ጋር አብረው ለመሥራት መነጋገራቸውንም ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ከሁለት ወር ባጠረ ጊዜ ውስጥ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን አምርተን ወደ ገበያ እናቀርባለን ነው ያሉት።
በቀጣይነትም ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ ለስኳር ፋብሪካዎች እና ከበድ ያሉ ቴክኖሎጅዎችን ለሚፈልጉ የተለያዩ ፋብሪካዎች ምርቶችን ለመሸጥ እንሠራለን ብለዋል። ኢንዱስትሪው ከቢጃይ ኢንዱስትሪያል እና ኢንጂነሪንግ ሶሉሽን ጋር በመተባበር ፋብሪካዎችን አምርቶ ለአፍሪካ ገበያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉንም አቶ ዘላለም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!