የኑሮ ውድነትን ለከላከል በትኩረት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

20

ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በግብርና ቢሮ ከምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በአቅራቢዎች እና በገዥዎች መካከል የሰብል ምርት ትስስር ለማድረግ ውይይት አድርጓል። የውይይቱ ተሳታፊዎች የምርት መሸጫ ቦታ ችግር እንዳለ አንስተዋል። የተሰጡ የመሸጫ ቦታዎችም ለተገቢው አካል አልተሰጡም ነው ያሉት። የአገልግሎት አሰጣጡም የአገልጋይነት ስሜት ያለው እንዲኾን ጠይቀዋል።

አምራች እና ገዥን ለማገናኘት የትራንስፖርት መካተት እንደሚገባው፣ የሸማቾች ማኅበራት እና ዩኒየኖች ሥልጠና ማግኘት እንዳለባቸው እና ለሚደረጉ ግብይቶች ደረሰኝ ሊኖር እንደሚገባም አንስተዋል። የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ምርታቸውን በቀጥታ ለኅብረተሰብ እንዲደርስ በማድረግ የሠሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውም ተጠቅሷል።

ምርት ይዘው የሚጠብቁ እና የኑሮ ውድነት የሚፈጥሩ ነጋዴዎች በመኖራቸው መንግሥት ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባ አመላክተዋል። ምርቶች በአንድ ጊዜ ዋጋቸው ሲሰቀል ንግድ ቢሮ ሊቆጣጠር እንደሚገባ ተጠቁሟል። በየቦታው ያለው ቀረጥ እና ያለአግባብ ክፍያ ለዋጋ ጭማሪው ምክንያት እየኾነ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሮች ግብዓቶችን በውድ ገዝተው ምርቱን በጥራትም ኾነ በታማኝነት እያቀረቡ በገበያ ውድነቱ ግን ተጠቃሚ አይደሉም ነው ያሉት። የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አትክልት አሳቤ ቢሮው በበጀት ዓመቱ ሰባት ግቦችን ለማሳካት አቅዶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የኑሮ ውድነትን መከላከል፣ አምራች እና ሸማችን ማስተሳሰር አንደኛው ግብ መኾኑን ተናግረዋል።

ሕገ ወጥነትን በመከላከል የኑሮ ውድነትን የመቀነስ ሥራ ውጤቶች ቢኖሩም ገና መሥራትን የሚጠይቁ ጉዳዮች መኖራቸውንም አንስተዋል። የንግድ መሠረትን ለማስፋት ነጋዴዎችን የማብዛት፣ የገበያ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት የደላላ ጣልቃ ገብነትን ለማስወገድ በስምንቱ ሪጅኦፖሊታንት ከተሞች በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በጀት የገበያ ማዕከላት እየተገነቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

በመንግሥት አንድ ቢሊዮን ብር ተመድቦ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማስተሳሰር መቻሉንም ጠቅሰዋል። የተመረጡ ሰብሎችን ማስተሳሰር እና በምን መንገድ እንደሚፈጸም አሠራር ማበጀት ይገባል ነው ያሉት። የደላላን ጣልቃ ገብነት መቀንስ እና ማስወገድ እንደሚገባም አንሰተዋል።

ኅብረተሰቡ፣ አምራቹ እና የንግዱ ማኅበረሰብም የንግድ ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ለሚያደርገው ጥረት ተባባሪ መኾን እንደሚገባው አሳስበዋል። በውይይቱ ማጠቃለያ የግብርና እና የኢንዱስትሪ አምራቾች ከአከፋፋዮች እና የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር የገበያ ትስስር ውል ተዋውለዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሳይንስ ዘርፍ የሴት ተመራማሪዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።
Next articleበኢኮኖሚው ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ሸማቾች መብቶቻቸው ሊከበሩላቸው እንደሚገባ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።