
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ ዘርፍ የሴት ተመራማሪዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ እና ችግር ፈቺ ምርምሮችን እንዲያካሂዱ ለማበረታታት ያለመ አውደርዕይ አካሂዷል።
በዩኒቨርሲቲው እየተካሄደ ባለው አውደርዕይ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሳይ ሙላቴ (ዶ.ር) “ሴት ተመራማሪዎች በሳይንሱ ዘርፍ ችግር ፈቺ ምርምር እንዲያደርጉ እንቅፋቶችን መጥረግ እና አጋር መኾን ያስፈልጋል” ብለዋል።
ካለው የሕዝብ ቁጥር ግማሽ ያህል ሴቶች በትምህርቱ ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ መኾኑን ተናግረዋል። ይህም ሴቶችን በማብቃት ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ ያሳያል ነው ያሉት። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሴት ተመራማሪዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።
ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በአውደርዕዩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል መሠንበት ሸንቁጥ ለሴቶች ምቹ ሁኔታ አሁንም እንደሌለ ገልጸዋል።
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለሴት ተመራማሪዎች ትኩረት የሰጠ አውደርዕይ በማዘጋጀቱ ምሥጋና አቅርበዋል። በመድረኩ ሴት ተመራማሪዎች ያከናወኗቸው የሳይንስ ምርምር ሥራዎች ቀርበዋል። ይህ ተሞክሮ ተጠናክሮ ለሌሎች ተመራማሪዎችም በር መክፈት እንደሚገባው ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ብርቱካን ማሞ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!