
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገንን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የጣና ዳር ንግሥቷ፣ ባለዘንባባዋ ሙሽራ፣ የቱሪዝም አስኳሏ ባሕር ዳር ሥራ ላይ ነች ብለዋል። ፍፁም የሰላም አየር፣ የዓይንና የመንፈስ ማረፊያ ውብ ሥፍራ የታደለችው ባሕር ዳር ከመዝናኛ እስከ ግዙፍ የንግድ ስፍራዎቿ በእንቅስቃሴ ተሞልተዋል፤ ሀገሬው ከጧት እስከ ማታ ሥራ ላይ ነው፡፡
የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ከልጅ እስከ አዋቂ በልዩ ልዩ ስፖርቶች ደምቀዋል፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ግዙፉ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መኾኑ ከተማዋን የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርጋት ይሆናል ነው ያሉት። ሀገሬው በሥራ የደከመ አካሉንና አዕምሮውን ለማደስ ስፖርት ሲሠራ፣ በመዝናኛ ማዕከላት ሲዝናና፣ በዘንባባዋ ጥላ ስር አረፍ ሲል፣ በጣና ዳርቻ ሰብሰብ ብሎ ሲጫወት፣ በምሽት በእግር ሲንቀሳቀስ ማየት ልብን ሀሴት ያወርሳል።
ወቅቱ የዐቢይና የረመዳን አፅዋማት የሚፆሙበት ነው። የከተማዋ ምዕመን ሰርክ ወደ መስጂድና ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሲተምም ማየት መንፈሳዊ ኩራትን ይፈጥራል። ውቧ ከተማ ልማቷን እያፋጠነች፣ ፍፁም የሰላም ድባብ፣ እረፍት አልባ የልማት ሥራ፣ ሞቅ ያለ የመዝናኛና የንግድ እንቅስቃሴ የሚታይባት ሆናለች ብለዋል።
ባየነው የሠላም ንፋስ የልማትና የሥራ ጥድፊያ፣ የቱሪዝም መነቃቃት ተደሰተናል። የተጀመሩ ሥራዎችን ዓይናችንን ሳንነቅል በተገቢው ጥራት እንዲጠናቀቁ ክትትላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!