
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ሂደት የብዙ ከዋኞችን ተሳትፎ የሚፈልግ የዲሞክራሲ እና የሰላም ግንባታ ሂደት ነው፡፡ ሂደቱ በርካታ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ኾኖ በተለያየ የዕድሜ ወሰን ውስጥ የሚገኙ፣ በተለያየ የሕይወት ተሞክሮ ውስጥ የሚያልፉ፣ እና በማኅበረሰባቸው ውስጥ የተለያየ ሚና የሚጫወቱ ዜጎችን ያሳትፋል፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያም እየተካሄደ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የትውልዶችን ተሳትፎ እና መስተጋብር በማበረታታት እና በጋራ ችግሮቻቸው ላይ መነጋገር እንዲጀምሩ በማድረግ አበረታች ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡
ሂደቱ በተለይም በአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ላይም ወጣቶች እና አረጋውያን ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመኾን እንዲወያዩ እና አጀንዳዎቻቸውን እንዲያዘጋጁ መፍቀዱ በትውልዶች መካከል የሚደረግን የምክክር ባሕል ለማስጀመር ያደረገው አንድ ወሳኝ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
ሂደቱ የተለያዩ ትውልዶች በሀገራቸው ጉዳይ ተቀምጠው ለመመካከር መፍቀዳቸው በመካከላቸው ያሉ የሀሳብ ልዩነቶች ወደ መሬት ወርደው ውይይት እንዲደረግባቸው ጋባዥ ሁኔታን ሲፈጥር ተስተውሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት ቀጥለው የቀረቡት ሀሳቦች በተለያዩ ትውልዶች መካከል የሚደረጉ ምክክሮች ሂደት የሚኖረውን ዋና ዋና ጠቀሜታዎች ያስረዳሉ፡፡
1. የጋራ ግንዛቤን በመፍጠር መግባባት ላይ ለመድረስ ማገዙ አረጋውያን፣ ጎልማሶች እና ወጣቶች በትላንቱ፣ በዛሬው እና በነገው የሀገራችን ጉዳይ ላይ በመነጋገር አንዱ በሌላው ያለውን የተዛባ አመለካከት በማጥራት በትውልዶች መካከል የተፈጠረን ክፍቶችን ለመሙላት ያግዛል፡፡ ይህም የተሻለ መቀራረብን፣ መነጋገርን ብሎም መግባባትን ይፈጥራል፡፡
2. የስሜት ሕመሞችን እና ጠባሳዎችን ለማከም ማገዙ በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች የተለያዩ ትውልዶች በሀገራችን ጉዳዮች ላይ ለመወያየት መፍቀዳቸው በሀገር ጉዳይ የተለያየ መስዋትነትን የከፈሉ፣ ጠባሳ ያለባቸው እና ለስነ ልቦና ሕመም ለተዳረጉ ጎልማሶች እና አረጋውያን ሕመማቸውን ለማከም በር ይከፍታል፡፡ ይህም ያለፈው ትውልድ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ያበረከተውን አስተዋፅኦ፣ ጀብድ እና ስህተቶችን አንስቶ ለመወያየት በር ስለሚከፍት የአሁኑ ትውልድም ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ላለፈው ትውልድ ሰብዓዊ ሀዘኔታን እንዲቸረው በማድረግ የስነ ልቦና ጉዳትን ለማከም በር ይከፍታል፡፡
3. አካታችነትን ማጠናከሩ የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ የሚፈልግ እና የሚያበረታታ የዲሞክራሲ ሂደት መኾኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በሂደቱ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች (ወጣቶች፣ ጉልማሶች እና አረጋውያን) መሳተፋቸው ሂደቱን ምሉዕ ለማድረግ የራሱን ሚና የሚጫወት ከመኾኑም በላይ አካታችነትን ያረጋግጣል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!