
ደሴ: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኮምቦልቻ ከተማ ፍቅር አንድነት እና ሰላምን የሚያፀና ልዩ የኢፍጣር መርሐ ግብር ተካሂዷል። የኢፍጣር መርሐ ግብሩ በታላቁ የረመዳን ፆም ወንድማማችነትን እና ሰላምን ለማጽናት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሀመድአሚን የሱፍ ወሎ አብሮነትን፣ መተሳሰብን፣ ፍቅርን በተግባር ኑሮ ያረጋገጠ አካባቢ በመኾኑ ይህንን አብሮነት የበለጠ ለማጎልበት ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ከክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ወንድም እህቶቹ ጋር የኢፍጣር መርሐ ግብር ማካሄዱን ገልጸዋል።
መርሐ ግብሩ ከአብሮነት እና ከዘላቂ ሰላም ግንባታ ባሻገር በከተማ አሥተዳደሩ ከሚዚያ 20/2017 ዓ.ም እስከ 29/2017 ዓ.ም ለሚካሄደው የኢንዱስትሪ እና የፋይናንስ ኤክስፖ ግብዓት እንደሚኾንም ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ እና ፋይናንስ ኤክስፖ መካሄዱ የቀጣናውን እምቅ የመልማት አቅም በማሳደግ ረገድ ፋይዳው የጎላ መኾኑንም ከንቲባው አስረድተዋል።
ኤክስፖው “ሰላም የኢንቨስትመንት ፓስፖርት ነው” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚካሄድም አብራርተዋል። በኢፍጣር መርሐግብሩ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ.ር)፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ታድመዋል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!