ፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር 78 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገቡን አስታወቀ።

24

ጎንደር: መጋቢት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት እና 23ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። የዩኒየኑ ሥራ አሥኪያጅ ይሁኔ ዳኘው የተቋሙን የ2015/2016 ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።

በ2015/16 የምርት ዘመን ዩኒየኑ 81 ሺህ ኩንታል የሰብል ግብይት ለማከናወን አቅዶ 13 ሺህ ኩንታል ግብይት ማከናወኑ ተገልጿል። በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በዕቅዱ ልክ ግብይት እንዳይካሄድ እንቅፋት መፍጠሩን ሥራ አሥኪያጁ ጠቅሰዋል። ለመንግሥት ሠራተኞች እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች በሦስት ወራት ክፍያ ጤፍ ማቅረብ እንደተቻለም ተጠቅሷል።

ዩኒየኑ በ13 ወረዳዎች፣ በ174 መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ከ145 ሺህ በላይ አባል አርሶ አደሮችን አቅፎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ተቋም ነው። አቶ ይሁኔ ዩኒየኑ 78 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገቡንም ገልጸዋል። ዩኒየኑ ለ2017/18 የምርት ዘመን በ2017 ግማሽ ዓመት 71 ሺህ ኩንታል ምርት ለመግዛት አቅዶ እስከ አሁን 7 ሺህ ኩንታል ተገዝቶ ለኅብረተሰቡ እየተሠራጨ ይገኛል ተብሏል።

በዩኒየኑ ፋብሪካ 91 ሺህ ሊትር ዘይት የተመረተ መኾኑን የጠቀሱት ሥራ አሥኪያጁ 280 ሺህ ሊትር አዲስ አበባ ካሉ የዘይት ፋብሪካዎች ትስስር በመፍጠር አስመጥቶ እያሰራጨ እንደሚገኝም አብራርተዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋሁን ተሰማ የክልሉ መንግሥት ለፀሐይ ዩኒየን ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበር 100 ሚሊዮን ብር ብድር ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።

የተገኘው ገንዘብ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተሠራበት መኾኑንም ጽሕፈት ቤት ኀላፊው ጠቅሰዋል። በተያዘው በጀት ዓመት 620 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑን የጠቀሱት አቶ ይሁኔ 165 ሺህ ኩንታል መቅረቡን አብራርተዋል። ከቀረበው ማዳበሪያ 75 ሺህ ኩንታል ወደ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት መሠራጨቱን ጠቅሰዋል።

የዩኒየኑ አባላት ያለፈውን ዓመት ዕቅድ ሪፖርት አድምጠው የቀጣይ ዓመት ዕቅድ ትውውቅን ገምግመው አጽድቀዋል።

ዘጋቢ፦ አገኘሁ አበባው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ።
Next articleያጋጠሙ ችግሮችን በጋራ በመሥራት ማለፍ እንደሚገባ ተገለጸ።