የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ።

85

ባሕር ዳር: መጋቢት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ.ር) ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር የቅድመ አደጋ፣ የአደጋ ወቅት እና ድህረ አደጋ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ፣ የፌደራል እና የክልል አሥተዳደር ተቋማትን የውስጥ አቅም ለመገንባት፤ ቅጽበታዊ አደጋ ሲከሰት እና ከአቅም በላይ ሲኾንም የአስቸኳይ ጊዜ እወጃ ሥርዓትን ለመዘርጋት እና ተግባራዊ ለማድረግ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የዘላቂ ልማት እና የሰላም ግንባታ እቅዶችን ለማስተሳሰር የሚያስችል የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ ለመዘርጋት እንዲያስችል የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ መኾኑን ገልጸዋል።

በረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክር ቤት መቋቋምን የተመለከቱ ድንጋጌዎች እና ስለ ኮሚሽኑ ተግባር እና ኀላፊነት፣ የምክር ቤቱ ሥልጣን እና ተግባራት፣ ስለፌዴራል መሪ ዘርፍ ተቋማት እና የክልል መንግሥታት ተግባር እና ኀላፊነት፣ ስለ አደጋ ተጋላጮች እና ተጎጂዎች መብት እና ግዴታ፣ ስለ ኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ መቋቋም የሚመለከቱ እና ሌሎች ድንጋጌዎች መካተታቸውንም ተናግረዋል።

ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 16/2017 ኾኖ በሙሉ ድምጽ ለውጭ ግንኙነት እና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍኖተ ሰላም ከተማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።
Next articleፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር 78 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገቡን አስታወቀ።